ከንቲባ አዳነች አቤቤ የማንሰራራታችን ሂደት ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችን የሚተርፍ ፣ ለዓለም የሚነገር ምስክርነት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት ዛሬ ለ2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ወደ አዲስ አበባ የመጡ ከ25 ሺህ በላይ እንግዶችን ተቀብለን በጉባኤው ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ጉባኤው “ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማሳለጥ፣ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ” በሚል መሪ ሀሳብ ከጳጉሜን 3 እስከ 5፣ 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል። በጉባዔው መሪ ሃሳብ መሠረት ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት መዛባት መፍትሔ ይሆናሉ ያለቻቸውን ተግባራት ጥንቅቅ አድርጋ እየሰራች መሆኗን በኤግዚቢሽን ተሳትፎአችን ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችን አስረድተናል።
እጅ ለእጅ ተያይዞ ለማደግ፤ ለመጪው ትውልድ የሚተርፍ ስራ ለመስራት አዲስ አበባ ማሳያ ተሞክሮዎችን ይዛ ቀርባለች ብለዋል፡፡
ውድ የከተማችን አንግዶች አዲስ አበባ የእናንተ የምቾት ቤታችሁ ናት ። አዲስ አበባ የእናንተ የብልፅግና በር ናት። መምጣታችሁ፣ አብረን መምከራችን ለመጪው የአፍካዊያን መፃኢ ዕድል መሠረት ነው ።
የከተማችን ነዋሪዎችም እስካሁን እያደረገችሁት ያለው አስተዋጽኦ ጉባኤው እስኪጠናቀቅና እንግዶች ወደየመጡበት አገር እስኪመለሱ ድረስ የተለመደ ትብብራችሁንና እንግዳ ተቀባይነታችሁን እንድታጠናክሩ ስል እጠይቃለሁ ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡