አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ የምትሻው እርዳታ ሳይሆን የጋራ ኢንቨስትመንት ነዉ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ

You are currently viewing አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ የምትሻው እርዳታ ሳይሆን የጋራ ኢንቨስትመንት ነዉ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ

AMN ጳጉሜን 3/2017

አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ የምትሻው እርዳታ ሳይሆን የጋራ ኢንቨስትምንት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ። ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄድ ጀምሯል።

በጉባኤው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)ን ጨምሮ የቀጣናውና የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ ተመራማሪዎች ተሳትፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናን ለመቋቋም ከጎደለን ሳይሆን ካለን መጀመር አለብን ብለዋል።

ከዚህ አኳያ አፍሪካ በርካታ የወጣቶች ቁጥር፣ መልማት የሚችል መሬት እንዲሁም ለታዳሽ ሃይል የሚሆን በርካታ አቅም አላት ነው ያሉት። በመሆኑም እዚህ የተገኘነው የዓለምን የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄ ለመቀየስ ነው ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። በመሆኑም አፍሪካ ስነ ምህዳሯን ሳትጎዳ ማደግ እንደምትችል አብራርተዋል።

አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ የምትሻው እርዳታ ሳይሆን የጋራ ኢንቨስትምንት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚደረግ ኢቨስትመንት ፋይዳው ጉልህ መሆኑን አንስተዋል።አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ዋነኛዋ መፍትሄ አመንጪ መሆን እንዳለባትም ተናግረዋል። አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የራሷን የመረጃ ሉዓላዊነት ሊኖራት እንደሚገባም አንስተዋል።

የአህጉሪቷ ዩኒቨርሲቲዎችና ተመራማሪዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈና ለአየር ንብረት ለውጥ የተደራጀ መፍትሄ የሚያቀርብ ማዕቀፍ እንዲቋቋምም ሃሳብ አቅርበዋል። ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ከ7 ዓመት በፊት በጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ አማካኝነት ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከሏንም ጠቁመዋል። የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከባቢን ከመጠበቅ ባሻገር የተጎዱ ከባቢዎች እንዲያገግሙ፣ ለምግብ ዋስትና እና ለስራ እድል ፈጠራ ትልቅ እድል መፍጠሩን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከአየር ንብረት ለውጥ ችግር መፍትሄ ጋር የተጣጣመ የመስኖ ልማት በማካሄድም በስንዴ ምርት ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቷን አብራርተዋል። በቅርቡ የሚመረቀው ታላቁ የህዳሴ ግድብም ከ5 ሺህ ዋት በላይ ታዳሽ ሃይል በማመንጨት ኢትዮጵያንና ቀጠናውን በሃይል ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ማስተናገድ እንደምትሻም ጠቁመዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review