ቃሜን ያደመቁት ሺኖዬ እና ጎቤ

You are currently viewing ቃሜን ያደመቁት ሺኖዬ እና ጎቤ

‎‎ወላሌ ወላሌ ሮቤ ያ ኮሎሌ

‎ያጋዲሴ ዱርባ ያጆሌ- ቃሜን ጌሴ  እያሉ የኦሮሞ ወጣት ልጃገረዶች የሺኖዬን መምጣት በዜማቸው የሚያሰሙበት ወቅት ነው።

‎ይህ ባህላዊ  ክንውን በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ቦታዎች እየተከበረ ሲሆን፤  እነዚህ ወጣቶች በአዲስ ሚድያ ኔትዎርክ በመገኘት የአዲስ አመት የመልካም ምኞታቸውን በዜማ በጭፈራ ከዚያም  በምርቃት ገልፀዋል።

‎አዲሱን ዘመን በአደባባይ እና ቤት ለቤት እየተዘዋወሩ የሚቀበሉበት ሲሆን፤ በሳምንቱም ለወራት ሳይገናኝ ተራርቆና ተነፋፍቆ የከረመን ዘመድ አዝማድ ወደ ሚያሰባስበው ታላቁ የኢሬቻ የምስጋና ቀን የሚያመሩበት የሚንደረደሩበት ነው፡፡ የአዲሱን ዓመት የመጀመሪያ ወር የገዳው ስርአቱ ቱባ ባህላዊ እሴት አንድ አካል አድርገው ይከውኑታል ሺኖዬ እና ጎቤ፡፡

‎በክረምት ወቅት ወንዞች ጢም ብለው መሙላታቸውን ተከትሎ  ለወራት ያልተገናኙ ጓደኛሞች፣ ጎረቤቶች እና ዘመድ አዝማዶች  የጳጉሜ ወር መድረሱ  ትልቅ ብስራት እንደሚሆንላቸው ይገለፃል ። የኦሮሞ ወጣት ልጃገረዶች  የሺኖዬን  በዓል የሚያከብሩት ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ነጥሏቸው የቆየውን ወንዝ መጉደል ተከትሎ ነው። ልጃገረዶቹ  የተሰሩት ሹሩባ ላይ   አዳ-ጀሌ አስረው  የቃሜን (ጳጉሜን)  ቀናት  አልፎ ፀደይ መግባቱን የሚያበስሩበት ቀን ነው ሺኖዬ።

‎ወጣት ብርሀኔ በየነ  ሺኖዬን ጨዋታ በኤ ኤም ኤን በመገኘት በዓሉን ካደመቁት መካከል አንዷ ናት። በስምንት አመት አንዴ የሚደረገውን የገዳ ስረዓት ምርጫ የሚገልፅ ሹሩባቸውን እንደሚሰሩ ታስረዳለች።

‎የገዳ ስረዓት ለማንፀባረቅ ስምንት ዘለላ ሹሩባ አራቱን በቀኝ አራቱን ደግሞ በግራ በማጠላለፍ የሚሰሩ መሆናቸውን የገለፀችው ወጣቷ፣  እጆቻቸው፣እግራቸው፣ ፀጉራቸው ጌጣጌጦችን (በጫጩ) በመጠቀም አምረው እና አሸብርቀው የሚታዩበት ወቅት እንደሆነ ገልፃለች።

‎በየአመቱ ከቃሜ ወር ጀምሮ በጉጉት የሚጠብቁት የሺኖዬ በዓል መሆኑን አስረድታ፣ እናቶቻች እና አባቶቻችን ያወረሱንን ባህል እና ትውፊት ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ በዘፈኖቻቸው ጭምር እንደሚያዜሙ ተናግራለች።

‎ይህንን ባህል  ለትውልድ ለማሸጋገር የሁሉም ሀላፊነት መሆኑን የገለፀችው ወጣቷ፣ ቤተሰብም ወላጆች ለልጆቻቸው ባህል ማስተማር እንዳለባቸው ገልጻለች። ኢትዮጰያ  የብዙ ህብረብሔራዊ አንድነት የሚንፀባረቅባት ባህል ያላት መሆኗን ገልፃ፣ እነዚህን ባህሎች ለትውልድ በማስተላለፍ በልዩነት ውስጥ ውበትን ማንፀባረቅ እንደሚቻል አስረድታለች።

‎እንደ እነዚህ ያሉ ባህሎች ውበት ጭምር ናቸው በማለት ተናግራለች። የጎቤ የአዲስ ዘመን ብስራት ባህላዊ ጨዋታውን ወንዶቹ ደግሞ ‎ቢኔሳ ማና – አና ሲፍ ወያ እያሉ ይጫወታሉ :: ጎቤ የኦሮሞ ወጣት ወንዶች ዘንድ ከሚናፈቁ የአደባባይ  በዓል ውስጥ አንዱ ነው ።

‎ክረምት መውጣትን ተከትሎ የልምላሜ እና የተስፋ ወራት ብራ ሲመጣ ግን ወንድ ወጣቶች ጎቤ እያሉ ሴት ወጣቶች  እየተዘዋወሩ የአዲሱን ዓመት መልካም ምኞታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ወጣት መገርሳ እና ከጓደኞቹ  በጎቤ ወቅት የአዲስ አመት መልካም ምኞታቸውን  ለአዲስ ሚድያ ኔትዎርክ  ለመግለፅ   ከመጡት መካከል አንዱ ነው። ወጣቱ  እንደሚለው ይህንን ባህል ለሚመጣው ትውልድ ማስተላለ እንደሚገባ ተናግሯል።  

‎በየአመቱ ባህሉን እና ትውፊቱን ለማስተዋወቅ  ከጳጉሜን ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት   አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ይከበራል ብሏል።   በዜማቸው አንድነትን አብሮነትን የሚገልፁ ሲሆን ከጭጋጋማው ክረምት ወደ ብራው ያሸጋገራቸውን አምላካቸውን የሚያመሰግኑበት ውቅት ነው ጎቤ።  እነዚህ ወጣቶች አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በመገኘት የአዲስ አመት መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

‎በሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review