በጥራት ለሃገር ኩራት የሆኑ እጆች

You are currently viewing በጥራት ለሃገር ኩራት የሆኑ እጆች

AMN -ጳጉሜን 03/2017 ዓ.ም

ሃገራት ኢኮኖሚያዊ ዓቅማቸውን ከሚያደረጁበት ዘርፍ አንዱ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ነው፡፡ ይህ ዘርፍ ሰፋፊ የስራ ዕድል ከመፍጠሩ ባሻገር ፈጠራን ለገበያ ለማቅረብ እና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡

ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ የተሻገረው ከወጭ የሚመረቱ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ወደ ሃገር ውስጥ የማስገባት ሁኔታ ባህል ሆኖ እየመጣ ነው ቢባል ማጋገን አይሆንም፡፡

በየዘመናቱ የውጭ ምርቶችን በራስ ዕውቀት እና ዓቅም ለማምረት እና ለመተካት በርካታ ጅምሮች ቢኖሩም፣ በፖሊሲ የተደገፈ ቀጣይነት ያለው ዘርፉን ከስር መሰረት ሊለውጥ በሚችል ደረጃ ተሰርቷል ለማለት ግን አያስደፍርም፡፡

ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን የማኑፋክቸሪንጉን ዘርፍ ገበያ ለማሟላት ከሚደረጉ የአነስተኛ ስራዎች ባሻገር በፈጠራ የዳበሩ ተወዳዳሪ ምርቶች ብቅ ብቅ ማለታቸው ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ከተሰጠው በርካታ ጥራት ያላቸው ምርቶታችን በራስ አቅም በማምረት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት የውጭ ምንዛሬን እና የቴክኖሎጂ እና ፈጠራ ባለቤት መሆን ይቻላል፡፡

በዚህም ሃገርን እና ህዝብን ተጠቃሚ በማድረግ የየዘርፉን ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይቻላል፡፡ ታዲያ ቀኑም ጳጉሜን 03/2017 ዓ.ም አይደል፣ እንደ ሃገር ዛሬ የእመርታ ቀን ነው፡፡ ባለፉት ሰባት ዓመታት እንደ ሃገረ በተሰሩ ስራዎች በርካታ ወጤት ማስመዝገብ ተችሏል፡፡

በበጋ ስንዴ የተጀመረው ስራና የመጣውን ውጤት እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል ፡፡ ውሃ፣ መሬት እና የሰው ሃይል በሞላባት ሃገር ስንዴን ከውጭ በማስገባት ዓመታት የመጣንበት ጉዞ በሁለት እና ሶስት ዓመታት ቀድሞ ስንዴ አብቃይ ከነበሩ አካባቢዎች ባሻገር፣ የስንዴ ምርት ተሞክሮባቸው በማያውቅ አካባቢዎች በተሰራው የበጋ መስኖ ከውጭ የሚገባን ስንዴ ለማስቀረት ውጤታማ ስራ መሰራቱ ማሳያ ነው፡፡

በሃገራችን በበርካታ አካባቢዎች የእንጨት ስራ/ፈርኒቸር/ በሃገራችን ከተጀመረ በርካታ ዓመታትን ያሰቆጠረ ቢሆንም፣ ነገር ግን ከዕለታዊ ገበያ ያለፈ ዓለም ዓቀፍ ተወዳዳሪ ምርት በማምረት ረገድ አመርቂ ምርት ማምረት ላይ ውስንነቶች ነበሩ፡፡

ታዲያ ይህንን ችግር ለመቅረፍና በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾችን ተወዳዳሪ በማድረግ ስራዎቻቸው ዓለም ዓቀፍ የጥራት ደረጃ መሰረት ያደረጉ በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን እንዲያመርቱ፣ መንግስት በፖሊሲ የተደገፈ ድጋፍ እና ክትትል በማድረጉ አሁን ላይ በርካቶች ተወዳዳሪነትን ማሳደግ ችለዋል፡፡

ከእነዚህ መካከል አቶ ሽፈራው ድረስ የሮቃ ፈርኒቸር ባለቤት እና ስራ አስኪያጅ አንዱ ናቸው፡፡ ከእንጨር ስራ ጋር የተዋወቁት በ1983 ዓ.ም ተቀጥረው በመስራት ሲሆን፣ ከ1987 ዓ.ም በኋላ የራሳቸውን ድርጅት በማቋቋም ሞያቸውን በማሻሻል ወደ ገበያወ መግባታቸውን ነው ያጫወቱን፡፡ ነገር ግን በግለሰብ ቦታ ተከራይቶ መስራት በሚፈልጉት ጥራት ያላቸውን ምርት ለማምረት ተቸግረው ዓመታትን አስቆጠሩ፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን በሚኖሩበት ወረዳ የነበሩ የዘርፉ የመንግስት መሰሪያ ቤት መደራጀት እንደሚችሉና መስሪያ ሼድ በመንግስት ድጋፍ እንደሚደረግላቸው የሚገልፅ የመስራች ይዘውላቸው መጡ ፡፡ ዕድሉንም በአግባቡ በመጠቀም ትላንት በአንድ ማሽን የጀመሩት የእንጨት ስራ አድጎ ዛሬ ላይ በጣም ዘመናዊ የሚባሉ ማሽኖችን ባለቤት ከመሆን ባለፈ ከውጭ የሚገቡ የእንጨት ስራ ውጤቶችን በማምረት ለዓለም ዓቀፍ ተቋማት ማቅረብ መቻላቸውን ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቆይታ አጫውተውናል፡፡

አሁን ላይ መንግስት በሁሉም ዘርፍ የሃገርን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማስመዝገብ እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ ነው የሚሉት አቶ ሽፈራው፣ በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ አካላት ምርቶቻቸው ዓለም ዓቀፍ የጥራት ደረጃን የጠበቁ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ የመስሪየታ ቦታ ድጋፍና ክትትል እንዲሁም ምርቶቻቸወን እንዲያስተዋውና የገበያ ትስስር እንዲየገኙ የሚዘጋጁ የኢትዮጵያ ታምርት እና የተለያዩ ኤግዚብሽኖችን ላይ እንዲሳተፉ በመደረጉ ይበልጥ ምርቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁ ዕድል እንደፈጠረላቸው ነው አቶ ሽፈራው የነገሩን፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ልማት በቢሮና በክፍለ ከተማ ደረጃ የሚያደርግላቸው ድጋፎች ከፍተኛ መሆኑን የሚያነሱት አቶ ሽፈራው፣ አሁን ላይ ድርጅታቸው የሚያመርታቸው ምርቶች ለባለ ኮከብ ሆቴሎች፣ ለኤምባሲዎችና ለሃይማኖት ተቋማት እያቀረቡ መሆናቸውን ገልፀው፣ ስራዎቹም ዓለም ዓቀፍ ጥራትን የጠበቁ ናቸው፡፡

በዚህም በቅርቡ ከሃገር አልፎ ወደ ውጭ ለመላክ ዕቅድ ይዘው እየሰሩ መሆኑን ነግረውናል፡፡ ባለ ኮኮብ ሆቴሎች እና ኤምባሲዎች ያለ ቀረጥ የእንጨት ውጤቶችን የማስገባት ዕድል አላቸው፡፡ ነገር ግን የኛን የሃገር ውስጥ ምርት የመረጡት ከውጭ የሚገባውን በጥራት መተካት ስለቻለ ነው፡፡ ይህም መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት በተግባር መጠቀም ሰለቻልን ነው ሲሉ ነግረውናል፡፡

እስካሁን ለሰሯቸው ስራዎችም በኤምባሲዎች፣ በኢንተርናሽናል ሆቴሎች እና በመንግስት ተቋማት ምስጋናና ዕውቅና የተሰጣቸው መሆኑን ያወሱት አቶ ሽፈራው፣ ይህም መንግስት እና ህዝብ የሰጠንን አደራ ይበልጥ ጥራት ያላቸው ምርቶችን በማምረት በዓለም ገበያ በማቅረብ ከወጭ የሚገባውን ምርት በማስቀረት የሃገርን ስም ከፍ ማድረግ እንድንችል የቤት ስራ የሰጠ ነው ብለዋል፡፡
አቶ ሳሙኤል ታደሰ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የኢንዱስትሪ ልማት ፅህፈት ቤት የእንጨትና ብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ቡድን መሪ ናቸው፡፡

የሃገር ውስጥ አምራቾች ተኪ ምርት እንዲያመርቱ እያደረገ ያለው እገዛ እንደ ከተማ ብዙ የዘርፉ ተዋናያኖች ተጠቃሚ መሆናቸውን አንስተው፤ እንደ ክፍለ ከተማ በከተማ ደረጃ ተኪ የእንጨት ስራዎቸን በማምረት ግንባት ቀደም ከሆኑት አንዱ አቶ ሽፈራው ድረስ መሆናቸውን አንስተው፣ እስካሁን እየሰሩት ባለው ስራም በክፍለ ከተማና በከተማ ደረጃ ዕውቅና የተሰጣቸው መሆናቸውን ጠቅሰው መንግስት ባስቀመጠው የጥራት ደረጃ ምርት በማምረት ለገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

አቶ ሽፈራው ድረስ ባቋቋሙት ድርጅት ጥራት ያላቸው ተኪ የእንጨት ምርቶችን ከማምረት ባለፈ ከ20 በላይ ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚና ኮንትራት ስራ ዕድል መፍጠር ችለዋል፡፡

ታዲያ ኢትዮጵያ ለጀመረቸው የማንሰራራት ዘመን በተሰማሩት ሙያ ሁሉ ዓለም ዓቀፍ ተወዳዳሪ ምርት በማምረት እመርታን በማረጋገጥ እየተጉ ባሉ ዜጎች እና ድርጅቶች ወደ ታላቅነቷ ለመመለስ የሚደረገው ጥረት አሁን ቀጥሏል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review