በሕገ ወጥ የወርቅ፣የገንዘብና የጦር መሣሪያ ዝውውር ወንጀል ተሳታፊ የነበሩ 76 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

You are currently viewing በሕገ ወጥ የወርቅ፣የገንዘብና የጦር መሣሪያ ዝውውር ወንጀል ተሳታፊ የነበሩ 76 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

AMN ጳጉሜን 3 / 2017

በሕገ ወጥ የወርቅ፣የገንዘብና የጦር መሣሪያ ዝውውር ወንጀል ተሳታፊ የነበሩ 76 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መግለጫ፥ በሕገ-ወጥ የወርቅ፣ የጦር መሣሪያና የገንዘብ ዝውውር ወንጀል ተሰማርተው በነበሩ የውጭ ሀገር ዜጎች እና ኢትዮጵያውያን ላይ በአዲስ አበባ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሲዳማ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በጥብቅ ዲሲፕሊን የመረጃ ክትትል ሲደረግ ቆይቶ ከኅብረተሰቡ ጋር በመተባበር መረጃ እና ማስረጃ ተደራጅቶ በሕግ ቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ የወርቅ ማዕድን በሕገ ወጥ መንገድ በማምረት፣ በመሰወር እና በማዘዋወር፣ የሀገራችንን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦችን እንዲሁም ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎችን በማዘዋወር ወንጀሎች ላይ ተሳታፊ እንደነበሩ መግለጫው ጠቁሟል፡፡

አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና ከየክልሎቹ የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ባካሄደው ልዩ ኦፕሬሽን እስካሁን 45 የውጪ ሀገር ዜጎች እና 31 የሀገር ውስጥ በድምሩ 76 ተጠርጣሪዎችን በሕግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል፡፡

ተጠርጣሪዎች ላይ በተደረገ ብርበራ በሕገወጥ መንገድ የተከማቹ ግምታቸው ከ7ኪ.ግ በላይ የወርቅ ምርቶችና ጌጣጌጥ፣ የወርቅ ማቅለጫና መመዘኛ መሣሪያዎች እንዲሁም አቅጣጫ ጠቋሚ ጂፒኤስ እና ማጠቢያ ኬሚካሎች፣ የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች ማለትም 19,707,465 የኢትዮጵያ ብር፣ 285,797 የአሜሪካ ዶላር፣ 207,910 ዩሮ፣ 177,930 4,075 የቱርክ ሊሬ፣ 16 ድርሀምና ሌሎች የተለያዩ የውጪ ሀገራት የገንዘብ ኖቶች እንዲሁም የተለያዩ ጦር መሳሪያዎች የተያዙ ሲሆን፤ ለእዚሁ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች ሲጠቀሙባቸው ተከማችተው የተገኙ ነዳጅ የያዙ በርካታ በርሜሎች፣ ጄነሬተሮች፣ ተሽከርካሪዎች እና የተለያዩ ሀገራት ፓስፖርቶች፣ ላኘቶፖች እና ሰነዶች በኤግዝቢትነት መያዝ ተችሏል።

ይህ የወንጀል ድርጊት ሆን ተብሎ የማይክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለማዛባት እንዲሁም የዋጋ ግሽበት በማናር በማኅበረሰቡ ላይ ጫና በመፍጠር ኑሮውን ለማናጋት እና የሀገራችንን ኢኮኖሚ አደጋ ላይ ለመጣል ታቅዶ ሲሰራ እንደነበረ መግለጫው አመልክቷል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የወንጀል መረቡን ለመበጣጠስ ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን ተጨማሪ ክትትሎችን እና ጥናቶችን በማድረግ ኦፕሬሽኑን የቀጠለ መሆኑን ገልፆ ፤ይህንን በመረዳት ኅብረተሰቡ መሰል ሕገወጥ ድርጊቶችን በመጠቆም የተደራጁ ወንጀሎችን በመዋጋት ሂደቱ ላይ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ጥሪውን አቅርቧል።

በተጨማሪም ሁሉም የክልል መስተዳደሮች ያለ ፌደራል መንግስት እውቅና እንዲሁም ያለ ኢሚግሬሽን ሕጋዊ የስራ ፈቃድ ማንኛውም የውጭ ሀገር ዜጋ በየትኛውም አካባቢ በመሰል የስራ ዘርፍ ላይ እንዲሰማራ ጊዜያዊም ይሁን ቋሚ ፈቃድ መስጠት እንደማይቻል በመገንዘብ ይህ አይነት ሕገወጥ ተግባርን በመከታተል የወንጀል ድርጊቱን በመከላከል ሂደት ውስጥ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ አሳስቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review