በዓለምአቀፍ መድረኮች የአፍሪካን ድምጽ ለማስተጋባት የተቀናጀና የተናበበ የጋራ ሥራ እንደሚጠይቅ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ገለጹ።
ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በጉባኤው መክፈቻ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የአገራት መሪዎች የዓለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማት ኃላፊዎች፣ፖሊሲ አውጪዎች፣ ምሁራንና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በጉባኤው መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ከሁለት ዓመታት በፊት በናይሮቢ በተካሄደው የመጀመሪያው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ የመፍትሄው አካል ለመሆን በቁርጠኝነት እንደምትሰራ አቅጣጫ ማስቀመጧን አስታውሰዋል።
አህጉሪቷ የችግሩ ዋነኛ ተጎጂ እንደመሆኗ ጉዳቱን አስቀድሞ ለመከላከል አሰላለፏን መቀየር ይገባታል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በአፍሪካ ለአየር ንብረት ተስማሚ ኢኮኖሚ ለመገንባትና ግብርናና ኢንዱስትሪን ለአየር ንብረት ተስማሚ ለማድረግ አገራት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል።
ይሁንና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል አገራት የሚያደርጉት ጥረት ውጤታማ እንዲሆን ዓለምአቀፍ ትብብርን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እያደረገች ያለውን ጥረት በዓለምአቀፍ መድረኮች ለማስተጋባት የተቀናጀና የተናበበ የጋራ ሥራ መስራት የሚጠይቅ መሆኑንም ተናግረዋል።
የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስሮችን በማጠናከር የአየር ንብረት ለውጥን በዘላቂነት መከላከል የሚያስችሉ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ ያስፈልጋል ብለዋል።
የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሀሙድ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ መንግስት በአዲስ አበባ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ እንድንመክር መድረክ ስላዘጋጀ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።
አገራቸው ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ያላት አስተዋፅኦ አነስተኛ ቢሆንም ከፍተኛ ጉዳት እያስተናገደች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
በመሆኑም በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት ሶማሊያ ትብብሯን አጠናክራ ቀጥላለች ብለዋል።
ለዚህም ፖሊሲ በመቅረጽና ተቋማዊ ማዕቀፍ በማዘጋጀት እንዲሁም የአረንጓዴ አየር ንብረት ፈንድ በማቋቋም የተግባር እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ተናግረዋል።