ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ስብሰባ አፍሪካ በዓለም አቀፍ መድረክ በአንድ አቋም ድምጿን የምታሰማበት ውሳኔ የሚተላለፍበት እንደሚሆን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
የሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄድ ጀምሯል።
በመርሀ ግብሩ ላይ የኢፌደሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሀሙድ አሊ የሱፍ፣ የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የጅቡቲ ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጌሌ፣ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ፣ የእስዋቲኒ ጠቅላይ ሚኒስትር ሩስል ምሚሶ ድላሚኒ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ተቋማት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፣ በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ ስብሰባው አፍሪካ በቀጣይ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤዎች የጋራ አቋም እንዲኖራት የሚያስችል ነው።
በሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ስብሰባ አፍሪካ አህጉራዊ መፍትሔዎች ላይ ውይይት የሚደረግበት መሆኑን ገልጸዋል።
ስብሰባውን ለማዘጋጀት ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ እንደነበር ገልጸው፤ የአዲስ አበባ የመሪዎች ቃል ኪዳን በቀጣይ ኮፕ-30 ጉባኤ አፍሪካ በአንድ አቋም ድምጿን የምታሰማበት መሆኑን መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ከዛሬ ጀምሮ በቀጣዮቹ ሶስት ቀናት ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን፣ የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ተጠቃሚነት፣ ቅድመ ማስጠንቀቂያ እና አፍሪካ መር መፍትሔዎች ውይይት ይደረግባቸዋል።