የስነ ምግባርና የፀረ ሙስና ትግሉን በቅንጅትና በትብብር ማከናወን መቻሉ በመዲናዋ የታቀዱ የልማት ስራዎች በስኬት እንደተሰሩ ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ በ2017 በጀት አመት በኮሚሽኑና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅትና በትብብር ሲያከናውናቸው የቆዩ ተግባራትን እና የ2018 በጀት ዓመት እቅድን በጋራ ገምግሟል።
የአዲስ አበባ ከተማ ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀማል ረዲ፣ የፀረ ሙስና ትግሉ በኮሚሽኑ አቅም ብቻ የሚከናወን ባለመሆኑ፣ ይህን መሠል የቅንጅትና የትብብር ስራዎች ለፀረ ሙስና ትግሉ ስኬት ወሳኝ አበርክቶ አላቸው ብለዋል።
ከጥቂት አመታት ወዲህ አዲስ አበባ ከተማ ላይ እየታየ ያለው ሁለንተናዊ የእድገት ለውጥ ለሀገር ልማትና እድገት ሊውል የሚችል ሀብትን በአግባቡ ስራ ማዋል በመቻሉ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በ2018 በጀት አመትም ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማጠናከር የሕብረተሰቡን ተሳትፎ በማሳደግ ዘላቂ ልማት በከተማዋ እንዲመዘገብ እንሰራለን ብለዋል።
የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ትምህርትን በማስፋት፣ የአሰራር ጥናትን በማጥናት እንዲስተካከሉ በማድረግ ሙስናንና ብልሹ አሰራርን በመከላከል በመንግሥት አሰራር ግልፀኝነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን በጋራ እየሰራን እንገኛለን ያሉት ደግሞ የኮሚሽኑ ባለድርሻ አካላት ናቸው።
በእለቱም በ2017 በጀት አመት ከኮሚሽኑ ጋር ስራን በቅንጅት ሲያከናውኑ ለቆዩ ባለድርሻ አካላት የእውቅና የምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን በ2018 ዓ.ም በጋራ ለሚያከናውኗቸው ተግባራትም የትስስር ሰነድ ተፈራርመዋል።
በታምሩ ደምሴ