አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት በፋይናንስ መደገፍ ፍትህን የማረጋገጥ ጉዳይ መሆኑን የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሀሙድ አሊ የሱፍ ገለጹ።
ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ “ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማፋጠን፣ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
ኢትዮጵያና የአፍሪካ ህብረት በጋራ ባዘጋጁት ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የተለያዩ አገራት መሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ምሁራንና ተመራማሪዎች፣ የአለምአቀፍና አህጉራዊ ተቋማት ተወካዮችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ታድመዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሃሙድ አሊ የሱፍ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ የአየር ንብረት ለውጥ አፍሪካን በብዙ እየፈተነ ይገኛል።
ይህን አለምአቀፋዊ ተግዳሮት ለመከላከል አህጉሪቷ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገች መሆኗንም አንስተዋል።
ይሁንና አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተጽዕኖን ለመከላከል የምታደርገው ጥረት በቂ የፋይናንስ የቴክኖሎጂና የባለሙያ ድጋፍ እያገኘ አለመሆኑን ነው የተናገሩት።
አፍሪካ ለዓለም አየር ንብረት ለውጥ ያላት ድርሻ አነስተኛ ቢሆንም የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ መሆኗን ማመላከታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
አህጉሪቷ አለምአቀፉን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል ለምታደርገው ጥረት ሁለንተናዊ የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግ ፍትህን የማረጋገጥ ጉዳይ ነው ብለዋል።
በሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ አፍሪካውያን በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ድምጻቸውን በጋራ ከማሰማት ባለፈ ለመፍትሔው በግንባር ቀደምነት መስራት እንዳለባቸውም ነው ሊቀመንበሩ ያሳሰቡት።