ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በአብሮነት እና በአንድነት ማሸነፍ እንደሚቻል በተግባር የታየበት ነው ሲሉ የሐረር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለምረቃ መብቃቱን ተከትሎ በሐረር ከተማ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የሐረሪ ብሄራዊ ጉባዔ ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አሚና አብዱልከሪምና በብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አብዱልሀኪም ኡመርን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ከሁሉም የከተማና የገጠር ወረዳዎች የተውጣጡ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
ተሳታፊዎቹ በድጋፍ ሰልፉ “ታላቁ የኢትዮዽያ ሕዳሴ ግድብ የኩራታችንና የአንድነታችን ማሳያ ነው፤ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ማሳያ ነው” የሚሉ እና ሌሎች መልዕክቶችን በማሰማት ደስታቸውን ገልጸዋል።
ከሰልፈኞቹ መካከል ወጣት ዙቤር መሐመድ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለምረቃ በመብቃቱ እጅግ ደስታ ተሰምቶኛል፤ ደስታውንም በአደባባይ በመውጣት ገልጸናል ብሏል።
የግድቡ ግንባታ የእኛነታችን መገለጫ እና በአንድነትና በአብሮነት ማሸነፍ እንደምንችል ያሳየንበት በመሆኑ ዛሬ ለእኔ ልዩ ቀን ብሏል።
በእኔ ትውልድ ያየሁት ትልቁ የጀግንነት ምልክት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ነው ያለችው ትግስት ደፈረሱ ደግሞ፤ ግድቡ ለዚህ ምረቃ በመብቃቱ እጅግ ደስታ ተሰምቶኛል ብላለች።
የግድቡ ለምረቃ መብቃት ለቀጣይ ስራዎቻችን በአብሮነትና በጀግንነት እንድናስቀጥል መነሳሳትን ፈጥሯል ስትል ተናግራለች።
ታላቁ የኢትዮዽያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የዘመናችንና የሀገራችን ትልቁ ፕሮጀክትና ድል ነው፤ እንደብሔራዊ ድላችንም እያከበርን ነው ያለው ደግሞ ወጣት ዓሊ መሐመድ ነው።
ግድቡ ለምረቃ በመብቃቱም እንደ አንድ ኢትዮዽያዊ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል ሲል ገልጿል።
ወይዘሮ ሂንዲያ አህመድ በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአብሮነት እና በአንድነት ማሸነፍ እንደሚቻል በተግባር ያሳየንበትና ቀጣዩ ትውልድም በተባበረ ክንድ ለመስራት ማነሳሳትን የፈጠረ መሆኑን መናገራቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በኢትዮዽያውያን የተባበረ ክንድ የተገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለምረቃ በመብቃቱ ደስታ ተሰምቶኛል ያለው የባለ ሶስት እግር አሽከርካሪው ፋሚ ዱሪ ነው።