ታላቁን የህዳሴ ግድብ ኢትዮያዊያን በቁጭት የገነቡት የጋራ አሻራቸው መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ

You are currently viewing ታላቁን የህዳሴ ግድብ ኢትዮያዊያን በቁጭት የገነቡት የጋራ አሻራቸው መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ

AMN – ጳጉሜን 4/2ዐ17 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አበቤ፣ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያዊያን በደማቸው፣ በላባቸው፣ በገንዘባቸውና በጉልበታቸው በቁጭት የገነቡት የጋራ አሻራቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በጋራ ርብርብ የገነባነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ፣ ለኢትዮጵያዊያን ትልቁ የጋራ ሀውልት እንደሆነም ነው ከንቲባ አዳነች አቤቤ የገለጹት፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የታሪካችን እጥፋት ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ ይህ ታሪክ ከእንግዲህ ወደ ኋላ የማይመለስ እና የማይበረዝ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ዳግማዊ አድዋችን ነው ብለዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች አክለውም፤ ስንተባበር እና በጋራ ስንቆም እንዲህ አይነት የታሪክ እጥፋትን በታሪካችን ውስጥ እንጽፋለን ብለዋል፡፡

የህዳሴ ግድብ በ14 አመታት ጉዞው በርካታ ችግሮች አጋጥመውት የነበረ ሲሆን፤ በእልህና በቁጭት በአይበገሬነት፣ በኢትዮጵያዊያ ላብ፣ ደም፣ ሀብት፣ ገንዘብ፣ ዕውቀትና የሃሳብ አመንጪነት በእንችላለን መንፈስ የተገነባ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን በአንደነት ከቆምን እንችላለን፤ ደግሞም ችለን አሣይተናል ያሉት ከንቲባዋ፣ ለዚህም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህያው ምስክር ነው ብለዋል፡፡

የውሃ ምንጫችን ህዳሴ ተገድቧል ያሉት ከንቲባዋ፤ አሁን ደግሞ የሚያስፈልግን ፍትሃዊ የባህር በር ጥያቄ በጋራ ቆመን ማስመለስ አለብን ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ህዳሴን ገነባን ብለን ልንቆም አይገባም፤ ይቻላልን ታጥቀን ከፊታችን ያለውን የብልፅግና ጉዞ ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ እስክትበለጽግ ድረስ በቁጭትና በእልህ እጅ ለእጅ ታያይዘን መጓዝ እንዳለብን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አመላክተዋል፡፡

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review