የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ባህል እየሆነ መምጣቱን ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ ገልፀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ባህል እየሆነ መምጣቱንና ለዚህም የቃሊቲ የውሃና ፍሳሽ ማጣሪያ አንዱ ማሳያ ስለመሆኑ ገልፀዋል።
ምክትል ከንቲባው ከዓለም ባንክ ሲንየር ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚስተር ኤግዚል ቫን ትራትስንበርግ ጋር የቃሊቲ ውሃና ፍሳሽ ማጣሪያ ማዕከልን ጎብኝተዋል፡፡

ከተማዋ በትኩረት ከምትሰራባቸው ዘርፎች መካካል የውሀ እና ፍሳሽ ማጣሪያ ልማት ስራ ግንባር ቀደም መሆኑን በጉብኝቱ ወቅት አንስተዋል።
በእዚህም መሰረት የፍሳሽ አወጋገድን ለማዘመን በኮሪደር የሚለሙ አካባቢዎችን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ዘመናዊ የፍሳሽ ማጣሪያዎችን እየገነባ እንደሚገኝ ተገልጿል።
የንፁህ ውሃ ፕሮጀክቶችን ለመስራት ከዓለም ባንክ እና ሌሎች ዓለም ዓቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በመቀናጀት መስራት እንደሚገባ አቶ ጃንጥራር አብራርተዋል።
ከተማዋ በዘርፉ የምትሰራውን ስራ ያደነቁት የዓለም ባንክ ሲንየር ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚስተር ኤግዚል ቫን ትራትስንበርግ በበኩላቸው ተቋማቸው ከከተማ አስተዳደሩ ጋር የሚኖረውን ትብብር እንደሚያጠናክር ገልፀዋል።
በመቅደስ ደምስ