አርሜኒያ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ አልፎ ለቀጣናው ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚያስገኝ ገልጻለች።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በዛሬው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተመርቋል።
በኢትዮጵያ የአርሜኒያ አምባሳደር ሳሃክ ሳርጌሲያን እና የ17ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የብዝሃ ህይወት ጉባኤ(ኮፕ 17) ፕሬዝዳንት የሆነችው አርሜኒያ ዋና ተደራዳሪ አምባሳደር መኸር ማርጋሪያን ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ሁለቱም ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ዛሬ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመመረቁ በአርሜንያ ህዝብና መንግስት ስም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አምባሳደር ሳሃክ ሳርጌሲያን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከዓመታት ጥረት በኋላ ዛሬ መመረቁ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ደስታን የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
ግዙፉ ግድብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውም ነው ያመላከቱት።
የ17ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የብዝሃ ህይወት ጉባኤ(ኮፕ 17) ፕሬዝዳንት የሆነችው አርሜኒያ ዋና ተደራዳሪ አምባሳደር መኸር ማርጋሪያን ግድቡ ከኢትዮጵያ ባለፈ ቀጣናዊ ፋይዳ ያለው መሆኑን መናገራቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ግድቡ የብዝሃ ህይወት ጥበቃ እና ዘላቂነት ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው አርሜንያ እ.አ.አ በ2026 በምታካሂደው በኮፕ 17 ፕሮጀክቱን እንደምታስተዋውቅ ገልጸዋል።