ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ነገዋን እየሠራች መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ

You are currently viewing ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ነገዋን እየሠራች መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ

ኢትዮጵያ ነገዋን ዛሬ ላይ ለመሥራት እያደረገች ያለውን ጥረት እና የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስተዋወቅ 5ኛዉን የጳጉሜን ቀን “የነገዉ ቀን” በሚል ስያሜ እና “ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ማድረግ” በሚል መሪ መልእክት እያከበረች ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከራሷ ባሻገር የአፍሪካን ማንሰራራት ለማብሰር ዛሬ ላይ ነገዋን እየሠራች ነው፡፡

ለአምስተኛዉ የኢንዱስትሪ አቢዮት የሚመጥን ትውልድ መቅረጽን፣ ለኢንዱስትሪ ዕድገቱ የሚመጥን ታዳሻ ኃይል ማቅረብን፣ የዘመኑ ከተሞችን መፍጠርን፣ ዐዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና እሳቤዎችን መቅረጽን ትኩረት ሰጥታ ለነገዋ እየሠራች ነው፡፡ ለትውልድ ዕዳን በማቅለል ምንዳ ለማውረስ እየተጋች ነው፡፡

ኢትዮጵያ ነገን ዛሬ ስትሠራ ለሌሎች አፍሪካውያን ጭምር የሚያሻግር እሳቤን በመያዝ ነው፡፡ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ዕቅዷን አሳክታ ወደ ቀጣዩ ስትራቴጂክ ዕቅድ ትግበራ ገብታለች፡፡ የነገዋን ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ የዜጎችን ማንነት በተሟላ መልኩ ማወቅ አንዱ ትኩረት ነው፤ ለዚህም የብሔራዊ መታወቂያ አገልግሎት ተጠቃሽ አብነት ነው፡፡

እስከዛሬ ባለው መረጃ መሠረት ከ23 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ለብሔራዊ መታወቂያ አገልግሎት ተመዝግበዋል፡፡ ይህንን በአጭር ጊዜ በብዙ እጥፍ ለማሳደግ እየተሠራ ነው፡፡ ዜጎች ፈጣን፣ ፍትሓዊና ከአድሎአዊ አሰራር የፀዳ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያግዝ ይሆናል፡፡ የ5 ሚሊዮን ኮደርስ ሥልጠናም ሌላው የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ ማሳለጫ መንገድ ነው፡፡

የፋይናንስ ዘርፉ በትሪሊዮን ብሮች በዲጊታል ግብይት ውስጥ እያሳለፈ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ጅምሮች የነገዋን ዲጂታል ኢትዮጵያ ታሳቢ ያደረጉ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል አስተማማኝ አቅርቦቷ ምክንያት የበርካታ ዳታ ማይኒንግ ኩባንያዎች መዳረሻ ሆናለች፡፡ የሞባይል ተጠቃሚዎች ቊጥር ከ85 ሚሊዮን 400 ሺህ አልፏል፡፡ ከ28 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን የሳይበር ደኅንነት ለማረጋገጥ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች በእጅጉ ስኬታማና ተስፋ ሰጪ ናቸው፡፡

በአፍሪካ ቀዳማዊዉ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ወደ ሥራ ከገባ ዓመታት ተቈጥረዋል፡፡ እነዚህ ኹሉ የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ ማሳያዎች እና የመዳረሻ መንገዶች ናቸው፡፡

የግብርና ምርምር ማእከላት እየተስፋፉና ዐዳዲስ ዝርያዎችን እያወጡ ነው፤ ይህም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እና ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች የሚያስከትሉትን ቋሚና ጊዜያዊ የምግብ ዋስትና ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያስችል ነው፡፡ የወጣቶችን ክሕሎት በአጫጭር ሥልጠናዎች በመገንባት በሀገር ውስጥ እና በውጭ አገራት በቴክኖሎጂ የታገዙ የሥራ ዕድሎችን እንዲያገኙ እየተሠራ ስኬትም እየተመዘገበ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዛሬ ፍላጎትና ፈተናዎች ብቻ ላይ አታተኩርም፣ ይልቁንም በሁሉም መስክ ለነገዋ መሰረት የሚጥሉ ታሪካዊ እርምጃዎችን እየተራመደች ነው፡፡

እንኳን ለነገዉ ቀን አደረሳችሁ!

ጳጉሜን 5/2017 ዓ.ም

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review