የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መመረቅና የኢትዮጵያ አዲስ ዓመትን አስመልክቶ የደስታ እና የመልካም ምኞት መግለጫ አስተላልፏል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ ተጠናቆ ለምርቃት ሲበቃ፤ ሀገራዊ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ጂኦፖለቲካዊ ፋይዳ ያላቸውን የልማት አውታሮችን የመገንባት እና ዓለም አቀፍ ሀብቶችን በህጋዊ እና ሰላማዊ መንገድ አልምቶ በፍትሀዊነት የመጠቀም እምቅ አቅም እንዳለው ለመላው አለም የተግባር ትምህርት እያስተማረ እንደሆነ ትልቅ አስረጅ መሆኑን ምክር ቤቱ ገልጿል፡፡
በመሆኑም በሀገሪቱ የዘመን መለወጫ ዋዜማ ላይ ሆነን ለኢትዮጵያ አንድነት የህዳሴ ግድብ የመመረቅ ደስታን እያጣጣምን፤ አዲሱን አመት በታላቅ ተስፋ መቀበል ብቻ ሳይሆን፣ ይህ ታላቅ ብስራት ለሀገሪቱ ትልቅ ድል ብቻ ሳይሆን አዳዲስ እድሎችን ይዞ እንደመጣ እንገነዘባለን ሲል ምክር ቤቱ ገልጿል።
በተጨማሪም የግድቡ መጠናቀቅ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፋይዳ እንዳለው ምክር ቤቱ አመላክቷል፡፡
ዐባይ ብቻ ሳይሆን የቀጠናውን ሀገሮች እና ህዝቦችን የሚያስተሳስሩ ሌሎች ዓለም አቀፍ ሀብቶችንም የዓለም አቀፍ ህግ በሚፈቅደው አግባብ አልምተን የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ማረጋገጥ ይገባናል የሚል የማይናወጥ አቋም እንዳለውም በመግለጫው አስታውቋል፡፡
ምክር ቤቱ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ መመረቅና ለአዲስ ዘመን መለወጫ በዓል እንኳን አደረሳችሁ ሲል መልካም ምኞቱን አስተላልፏል፡፡
በአንዋር አህመድ