ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም የሚያስችል ሶስተኛውን የአስር ዓመት ዕቅድ ይፋ አደረገች

You are currently viewing ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም የሚያስችል ሶስተኛውን የአስር ዓመት ዕቅድ ይፋ አደረገች

AMN ጳጉሜን 5/2017

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም የሚያስችል ሶስተኛውን የአስር ዓመት ብሔራዊ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የአየር ንብረት ለውጥ ዕቅድ ይፋ አደረገች።

ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ስብሰባ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄድ ከጀመረ ሶስተኛ ቀኑን ይዟል።

በመርሀ ግብሩ የአፍሪካ የአየር ንብረት ተፅዕኖን ለመቀነስ በግብርና፣ አፈር ማዳበሪያ፣ ታዳሽ ሀይል፣ የአየር ንብረት ፋይናንስ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት የሚያስችሉ ውይይቶች እየተደረጉ ነው።

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት የበካይ ጋዝ ልቀትን በመቀነስ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም የሚያስችል ሶስተኛ የአስር ዓመት በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የአየር ንብረት ለውጥ ዕቅድ ይፋ አድርጓል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን ፕሮጀክትቱን ይፋ ባደረጉበት ወቅት፤ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የአየር ንብረት ለውጥ ዕቅድ በፓሪስ ስምምነት መሰረት በየአምስት ዓመቱ ማሻሻያ ይደረግበታል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የአየር ንብረት ለውጥ ዕቅድ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2025 እስከ 2035 የሚቆይ መሆኑን ገልጸዋል።

ዕቅዱ ከኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር፣ ከሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው፣ ከ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ እና በረጅም ጊዜ የካርበን ልቀት ልማት ስትራቴጂ 2050 ጋራ የተጣጣመ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2019 እስክ 2023 በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር አማካኝነት የደን ሽፋን ከ6 ነጥብ 4 ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልጸው፤ በ2030 ወደ 30 በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል ብለዋል።

የአስር ዓመቱ ዕቅድ የግብርና ምርታማነትን፣ የከተማ መሰረተ ልማትን፣ የታዳሽ ሀይል አቅርቦትን እና የሰብል ምርታማነትን ተጨባጭ በሆነ መንገድ የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረዋል።

በዶሮ እርባታ፣ ንብ በማነብ፣ በስጋ ምርት እንዲሁም በመስኖ ልማትና በሌሎች የግብርና ዘርፎች የተመዘገቡ ለውጦችን ማስቀጠል እንደሚችል ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለብዝሀ ህይወትና ሥነ ምህዳር ጥበቃ፣ የመሬት መሸርሸርን ለመከላከልና ጠንካራና ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚ ለመገንባት ከፌደራል ዓመታዊ በጀት እስከ አንድ በመቶ የሚሆነውን ትመድባለች ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ይጠይቃል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ዕቅዱን ለማሳካት 98 ነጥብ 35 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በመሆኑም ለዕቅድ መሳካት ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ በፋይናንስ፣ በቴክኒክ እና በቴክኖሎጂ ዕገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review