ለአዲስ አመት ዋዜማ በሚደረጉ ግብይቶች ማህበረሰቡ በሀሰተኛ የብር ኖቶች እንዳይጭበር ጥንቃቄ እንዲያደርግ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ተናግረዋል።
ኮማንደር ማርቆስ በበዓል ወቅት ከሚፈፀሙ ወንጀሎች መካከል ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ወንጀል የሚፈፀመው በሁለት አይነት መልኩ መሆኑን ተናግረዋል።
የመጀመሪያው ሙሉ ለሙሉ ሀሰተኛ የብር ኖቶች ወደ ገበያ ይዘው የሚመጡ ሊኖሩ እንደሚችሉ፤ በሁለተኛነት ደግሞ ህጋዊውን ከሀሰተኛ ጋር የብር ኖቶች ጋር በመቀላቀል ወደ ገበያ የሚያመጡ ግለሰቦች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ህብረተሰቡ የእነዚህ ወንጀሎች ሰለባ እንዳይሆን ከሚያደርገው ጥንቃቄ በተጨማሪ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥመው በአቅራቢያው ወደሚገኝ የጸጥታ አካላት መጠቆም ይገባል ሲሉ ኮማንደር ማርቆስ ተናግረዋል።
በበዓል ዋዜማ ወቅት በሚበሉ እና በሚጠጡ ምግቦች ባዕድ ነገሮች የሚቀላቅሉ ግለሰቦች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ህብረተሰቡ በተለይም ዘይት፣ ቅቤ፣ በርበሬ እና ሌሎችም የበዓል ግብዓቶችን ሲሸምት ጥንቃቄ ማድረግ እንሚገባው አንስተዋል።
ከዚያ ውጭ ቅሚያዎች ፣ ማታለሎች እና በተለምዶ ሿሿ የወንጀል ድርጊቶች በዚህ ወቅት ሊፈፀሙ ስለሚችሉ ህብረተሰቡ ከእነዚህ ወንጀሎች ራሱን እንዲጠብቅ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል ።
እነዚህ ወንጀሎች እንዳይፈፀሙ ጥንቃቄን ገንዘብ ማድረግ አለብን ያሉት ኮማንደር ማርቆስ ናቸው።
የትራፊክ አደጋ መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ መሆኑን የገለፁት ኮማንደር ማርቆስ፤ በዓልን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለማክበር ወደ አዲስ አበባ የሚመጡና የሚወጡ ዜጎች በስራ ጫና ቀኑን አሳልፈው የሌሊት ጉዞ የሚያደርጉ መኖራቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት የሌሊት ጉዞ ለአደጋ የሚያጋልጥ በመሆኑ፤ ያልታቀዱ ወይም ለትራፊክ አደጋ ከሚያጋልጡ ጉዞዎች እራሳቸውን እንዲጠብቁ አሳስበዋል።
በበዓል ወቅት ከተለያዩ አደጋዎች እና ማጭበርበሮች ማህበረሰቡን ለመጠበቅ የአዲስ አበባ ፖሊስ መምሪያ፣ ፌደራል ፖሊስ ፣ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት፣ ትራፊክ ፖሊስ እና ሰላም እና ፀጥታን በመዲናዋ መሰማራታቸውን ገልፀዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ የሸገር ከተማ አስተዳደር የፀጥታ አካላት በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የሚተላለፉትን የጥንቃቄ መልዕክቶች ህብረተሰቡ ወደ ተግባር መቀየር አለበት ብለዋል።
በሔለን ተስፋዬ