ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የኅብረትና የትጋት ውጤት መሆኑን የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም የገነቡትን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ትናንት በይፋ መርቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ(ኢዜማ) ምክትል መሪ አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያውያን ኩራት ነው ብለዋል፡፡

ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን ያለ አንዳች ልዩነት በጋራ ተባብረው እውን ያደረጉት ፕሮጀክት እንደሆነ አንስተው የአሁንና የመጭው ትውልድ የጋራ ሐውልት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ያለፈው ትውልድ ቁጭት ወደ ብስራት የተሸጋገረበትና ለመጪው ዘመን ትልቅ ተስፋ የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ሙሉብርሃን ኃይለ፥ ሕዳሴ ግድቡ የኢትዮጵያውያን ደማቅ አሻራ ያረፈበትና ገጽታን የሚቀይር ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን ተናግረዋል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከጫፍ ጫፍ የተሳተፈበት በመሆኑም የዘመናችን ዓድዋ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮቹ እንደገለጹት ግድቡ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በትብብር መፈጸም መቻላችን ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በሕብረት ለማከናወን ትልቅ ስንቅ የሚሆን ነው፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካውያንን የመፈጸም አቅምና ያላቸውን የተፈጥሮ ሃብት ተጠቅመው መልማት እንደሚችሉ ማሳያ እንዲሁም የቀጣናው ሀገራትና አፍሪካውያን በዓለም መድረኮች በኩራት የሚያነሱት ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑን ነው የገለጹት።
የፖለቲካ ፓርቲዎችም በሐሳብ እየተፎካከሩ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ በጋራ መረባረብ እንደሚያስፈልግ መናገራቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድቡ ሁሉ በሌሎችም ሀገራዊ ጉዳዮች በጋራ ልንቆም ይገባል ብለዋል፡፡