በበዓል ዋዜማ ወቅት ከሚደርሱ ድንገተኛ አደጋዎች ህብረተሰቡ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የአዲስ አበባ ከተማ የእሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ የእሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ፣ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል እንደተናገሩት፤ በዘመን መለወጫ በዓል ዋዜማ ወቅት ምግብ ለማብሰል እና ሌሎች ስራዎችን ለመከወን የኤሌክትሪክ ሀይል ፍጆታ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ ሀይል እና የከሰል አጠቃቀም ላይ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የመዲናው ነዋሪዎች በበዓል ወቅት ሊኖር ከሚችለው የአደጋ ተጋላጭነት እራሳቸውን እንዲጠብቁ ሲሉ የጥንቃቄ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በተለይም ሁሉንም የበዓል ስራዎች በተመሳሳይ ሰዓት መከወን ለአደጋ አጋላጭ በመሆኑ፣ ስራዎችን በቅደም ተከተል በማድረግ ሊደርሱ የሚችሉ አደጋዎችን መቀነስ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ኮሚሽኑ ከበዓሉ አስቀድሞ ሕዝብ በስፋት በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በስፋት ከማከናወኑን በተጨማሪ፣ በአደጋ ቅነሳ እና በአደጋ ምላሽ ዘርፍ አቅዶ ወደ ስራ መግባቱንም ጠቅሰዋል ።
ኮሚሽኑ በተለያዩ ሚዲያዎች በበዓል ወቅት አደጋ እንዳያጋጥም የቅድመ ጥንቃቄ መልክት ማስተላለፉን የጠቆሙት አቶ ንጋቱ፣ ከዚህ በተጨማሪ አደጋ ሲከሰት ምላሽ ለመስጠት ተዘጋጅቷል ብለዋል።
ማህበረሰቡ የቅድመ አደጋ የጥንቃቄ መልዕክቶችን በአግባቡ በመተግበር በዓሉ በሰላም እንዲያልፍ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ እና የተለመደውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አቶ ንጋቱ አስገንዝበዋል።
በበዓል ወቅት በመዝናኛ ስፍራዎች የትራፊክ እና መሰል አደጋዎች ቢያጋጥሙ ምላሽ ለመስጠት የአንቡላስ አገልግሎት የሚሰጡ ቡድኖች ተዘጋጅተዋል ብለዋል።
የእሳትና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ካጋጠመ በነጻ የስልክ መስመር 939፣ በቀጥታ የስልክ መስመሮች 0111-55-53-00 ወይም 0111-56-86-01 በመደወል ማሳወቅ እንደሚቻልም አቶ ንጋቱ ጠቁመዋል።
በሔለን ተስፋዬ