አዲስ መሶብ ትናንት ተመርቆ ስራ ጀምሯል
የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ለዜጎች ወቅቱን የጠበቀ፣ ግልጽ እና ተደራሽ አገልግሎት የማረጋገጥ ቁርጠኝነታችንን የሚያንፀባርቅ ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት ከአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከልን ከጎበኙ በኋላ በይፋዊ የማህበራዊ ገፃቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ነው፡፡
አክለውም፣ ማዕከሉ አገልግሎት አሰጣጥን፣ የመልካም አስተዳደር የማዕዘን ድንጋይ የማድረግ እና ለዜጎች ወቅቱን የጠበቀ፣ ግልጽ እና ተደራሽ አገልግሎት የማረጋገጥ ቁርጠኝነታችንን የሚያንፀባርቅ ነው ብለዋል፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው የህዳሴ ግድባችንን በመረቅንበት ማግስት ለህዝባችን የአገልግሎት እንግልት ምላሽ ለመስጠት፣ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል ብለዋል፡፡
እንደ ሀገር በርካታ የልማት ስራዎችን ሰርተናል ያሉት ከንቲባዋ፣ በተለይ አዲስ አበባ ላይ ሳምንቱን ሙሉ ለ24 ሰዓት እየተሰራ የከተማዋ ገጽታ የተቀየረበት፣ ተገልጋዩ ማህበረሰብ በብዙ መንገድ ተጠቃሚ የሆነበት ልማቶችን ውጤታማ ማድረግ ችለናል፡፡ ከዚያው ጎን ለጎን ደግሞ አገልግሎት መዘመን አለበት፣ ህዝቡ ቅሬታ የሚያሰማባቸው፣ የሚንገላታባቸውና ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት በኩል ያሉትን ድክመቶች ለማረም መሶብ አገልግሎትን አስጀምረናል ሲሉ አክለዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች በንግግራቸው አዲስ መሶብ የህዝባችንን እንግልት በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል፡፡ አሁን ለመጀመሪያው ዙር 13 ተቋማትን አስገብተናል ብለው፣ 107 የዲጂታል አገልግሎቶችን በዚህ ማዕከል እንደሚሰጥ ገልፀዋል፡፡
እነኚህ የመረጥናቸው ተቋማት ወይም የአገልግሎት አይነቶች አብዛኛው ህዝብ በብዛት አገልግሎት የሚፈልግባቸው እንደ የመሬት አገልግሎት፣ የመሬት ምዝገባ አገልግሎት፣ ገቢዎች፣ ንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር፣ ቤቶች ኮርፖሬሽን፣ ቤቶች ልማት፣ ፋይዳ መታወቂያ፣ የሲቪል ምዝገባ፣ ፕላን… አንድ ላይ ተቀናጅተው አገልግሎት እንዲሰጡ ነው የተደረገውም ብለዋል፡፡
“አንድ ተገልጋይ በዚህ ማዕከል ወደ ሌላ ቦታ መሄድ አያስፈልገውም። የክፍያ ሰርቪስ የሚሰጡ ባንኮች፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ገብተዋል፤ በሂደት ላይ ያሉ ተቋማትም አሉ፡፡ እኛም 13 ተቋማትን እና 107 አገልግሎቶችን ብቻ አይደለም የምናስገባው፤ ሌሎቹም እየተሰራባቸው ናቸው፡፡ በየጊዜው እየጨመርን ነው የምንሄደው፡፡ ሌሎቹ አገልግሎቶች ሲመጡ የሚገቡባቸው ምቹ ቦታዎችም ተዘጋጅተዋል፡፡ አገልግሎቶቹን ወደ ማዕከል እያስገባን እንሄዳለን፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ከሁሉ በላይ ለህዝብ በቅርበት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለን በየክፍለ ከተማው ይህን አገልግሎት ስናወርድ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ክፍለ ከተማ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ይኖረናል። አራዳ ክፍለ ከተማ ከዚሁ የሚሰጥ ነው የሚሆነው፡፡ ከአንድ ሳምንት በኋላ ደግሞ የቦሌ ክፍለ ከተማን እንመርቃለን። በመቀጠልም 9ኙ ክፍለ ከተሞች ወደ አገልግሎት እንዲገቡ የሚያስችሉ ስራዎች በመሰራት ላይ ናቸው፡፡ ይህን ማድረግ ከቻልን ለህዝባችን ትልቅ ብስራት ነው። ዛሬ የመረቅነውም የአዲስ ዓመት ስጦታችን ነው፡፡”
ዛሬ የተመረቀው የአንድ ማዕከል አገልግሎት የሚገኝበት ቀደም ሲል አራዳ ክፍለ ከተማ የነበረ እና ለከተማችን ማዕከል የሆነ ቦታ ነው የመረጥነው ያሉት ከንቲባዋ፣ “በቂ የመኪና ፓርኪንግ አለ፤ ለባለጉዳዮችም ሆነ ለሰራተኞች የሚያገለግሉ የህጻናት ማቆያ ቦታዎች አሉ፤ የካፍቴሪያ አገልግሎቶች አሉን፡፡ ምንም አይነት እንግልት ሳይኖር አገልጋይና ተገልጋይ ፊት ለፊት ተገናኝተው አገልግሎትን ከአንድ ማዕከል፣ ከአንድ ቦታ ማግኘት የሚችልበት፣ ከፍተኛ የህዝብን እንግልት መቀነስ የሚችል፣ ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት መስጠት የሚያስችል፣ በፎርጅድና በመሳሰሉት ስንቸገርበት የነበረውን የማጭበርበር ስራዎችን ሊያስቀር የሚችል ትልቅ ማዕከል ነው፡፡ ህዝባችን እንኳን ደስ አላችሁ፡፡ አዳምጠን የህዝቡን ጥያቄ መመለስ የሁልጊዜ ስራችን ነው፡፡ አንዱ አዲስ ምላሻችንም ይኼው ነው፡፡”
ከተማችን ላይ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር አውጥተን ኢንቨስት ካደረግንባቸው መሰረት ልማቶች መካከል አንዱ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት ነው ብለው፣ ቴክኖሎጂ ለዘላቂ እድገት፣ ስማርት ሲቲ የመሆን መሰረት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተካልኝ አማረ