በዓሉን ስናከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን ይገባል ተባለ

You are currently viewing በዓሉን ስናከብር የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን ይገባል ተባለ

የአዲስ ዓመት በዓልን ስናከብር በፍቅር፣ በመተሳሰብ፣ በመተጋገዝ እና የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን ይገባል ሲሉ የኃይማኖት አባቶች ተናገሩ፡፡

የአዲስ ዓመት በዓልን አስመልክቶ የኃይማኖት አባቶቹ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፣ የአዲስ ዓመት በዓልን በአንድነት በመቆም ለተራቡት፣ ለተጠሙት፣ ለታረዙትና ለታመሙትም ሁሉ ካለን ከፍለን በመስጠት ከእኛ ጋር በመንፈስና በሞራል በዓሉን እንዲያሳልፉ እናድርግ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለኃይማኖት፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል እና የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ዋና ጸሐፊ ቄስ ደረጀ ጀንበሩ ለአዲስ ዓመት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለኃይማኖት በመልዕክታቸው፣ አዲሱን ዓመት መልካም በሆነ በአዲስ ሀሳብ፣ በመልካም ምግባር፣ በልማት፣ በሰላም፣ በፍቅር፣ በእርቅና በስምምነት እንድንቀበለው ጥሪ አቅርበው፣ “በተሰጠን ዕድሜና ዘመን ለኑሮአችን የሚያስፈልገንን ፍጆታ ለማግኘት ላባችንን አንጠፍጥፈን መስራት ይኖርብናል” ሲሉ መክረዋል፡፡

ፓትርያርክ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ አክለውም፣ በአዲሱ ዓመት ለሀገር ሰላምና ልማት፣ አለመግባባትን በእርቅ ለመፍታት ህዝባችን ጠንክሮ መስራት አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡

“አዲሱን ዓመት ለሀገር ሰላምና ልማት፣ ለህዝባችን አንድነትና ስምምነት እንደዚሁም አለመግባባትን በእርቅ ለመፍታት ከልብ የምንተጋበት መልካም የስኬት ዘመን እንዲሆንልን እንፀልይ። በዚህም መላው ህዝባችን ጠንክሮ እንዲሰራ አባታዊ መልዕክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን” ብለዋል ፓትርያርክ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፡፡

አክለውም፣ አዲሱን ዓመት በአዲስ እሳቤ ካላጀብነው አዲስ ሊሆን አይችልም ያሉት ፓትርያርኩ፣ ኢትዮጵያውያን ከግለኝነት አስተሳሰብ ወጥተን በእኩልነትና በአብሮነት ብንሰራ ያሳድገናል፤ በእጅጉም ይጠቅመናል፡፡ ይህንንም በአዲሱ ዓመት የምንመራበት እሳቤ አድርግን ልንወስደው ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው፣ አዲሱን ዓመት ወደ ሰላም በሚወስዱ ሀሳቦች፣ እቅዶችና ንግግሮች በማክበር እንጀምር ብለዋል።

ንግግራችን የሰዎችን ቁስሎች ይፈውሱ፤ ወደእርቅና አንድነት ይምሩን ያሉት ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ፣ መላው ምዕመን በዙሪያው ያሉትን ወገኖቻችንን ማስታወስ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ፣ በተለያዩ መልካም ተግባራት መጽናናትና የተሻለ ሕይወትን እናበርክትላቸው ብለው፣ ፈጣሪ አንዳችንም እንድንራብ አይፈልግም፤ በዘላቂ ሁኔታ ሰዎች ጠግበው የሚያድሩበትን ሁኔታ እንፈልግ፤ ለዚህም ተግተን እንስራ። አዲሱ ዓመት የተሰጠንን በጎ ነገሮችን እንድናስብና ለጋራ ጥቅም የሚሆኑ ተግባራትን እንድንፈጽም ነውና ለዚህ እንነሳሳ ሲሉም አስገንዝበዋል።

“በመላው ኢትዮጵያ እርቀ ሰላም ወርዶልን በፍቅርና በህብረት የምንኖርበት ዘመን ያድርግልን፡፡ አዲሱ ዓመት ለተራቡት፣ ለተጠሙት፣ ለታሰሩት፣ ለታመሙት፣ ለተሰደዱትና ላዘኑት የሚጽናኑበትና የሚደሰቱበት ጊዜ ይሁንላቸው።” ብለዋል ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ በአዲስ ዓመት መልዕክታቸው፡፡

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ዋና ጸሐፊ ቄስ ደረጀ ጀንበሩ ባስተላለፉት የ2018 ዓ.ም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፣ በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንኳን በሰላምና በጤና ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ ብለዋል፡፡

ያለፈው ዓመት ቀላል የማይባሉ ተግዳሮቶችን በብቃት የተወጣንበት ብቻ ሳይሆን ታሪክ የማይዘነጋው ታላቁ ጅማሬያችን ፍጻሜ ያገኘበት ዓመት መሆኑን በማውሳት፤ የመላው ኢትዮጵያዊያን የልብ አምሮት የነበረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተጠናቀቀበት ዓመት ስለሆነ ሁላችንንም እንኳን ደስ አለን፤ እንኳንም እግዚአብሔር ለስኬት አበቃን ሲሉ ምኞታቸውን ገልፀዋል፡፡

ይህ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለመጪው ትውልድ ኩራት የሚሆን አስደናቂ ስኬት ከመሆኑም በላይ በአንድነት የመቆም ጣፋጭ ፍሬ ምን ያህል እንደሚያረካና ዓለምን የሚያስደንቅ ድል እንደሆነ አፍ አውጥቶ በራሱ የሚናገር እና ለበለጠ ስራ የሚያነሳሳ እንደሚሆን  አንጠራጠርም ብለዋል፡፡

መጪው ትውልድ በአባቶቹ የሚኮራበት እና የሚዘክረው ታሪክ ለማብሰር አዲሱ ዓመት ጥላቻን እና ግጭትን የምንቀብርበት እና እውነተኛ ሰላምን በማስፈን ለህዝባችን የምስራች የምናበስርበት ዓመት እንዲሆን ከልብ ሁላችንም ልንነሳ ይገባልም ብለዋል፡፡

የህዝባችንን አንድነት በአስተማማኝ ዓለት ላይ ማቆም እና ዘላቂ ሰላምን ማስፈን ትኩረት ሊሆን ይገባል፡፡ ይህም  ካለፈው ታሪካችን በመማር ነገአችን ብሩህ ይሆን ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ከልብ በንስሐ ያለውን ልዩነት በይቅርታ በማስተካከል የእኛ የምንላትን ኢትዮጵያን እድገት ማፋጠን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ፕሬዝዳንት ቄስ ዮናስ ይገዙ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ባለፈው ዓመት የታዩትን ደካማና ጠንካራ ጎኖቻችንን በመለየት፣ ድክመቶችን በማስተካከልና ጥንካሬዎችን በማጎልበት አዳዲስ ርዕዮችን መሰነቅ ይገባል፡፡ ይህ ከሁሉም ዜጋ መልካም ስብዕናን ተግቶ መፈለግን የሚጠይቅ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ለዜጎች ኑሮ መሻሻል በሚደረገው ቀጣይ ጥረት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ በትጋትና በታማኝነት ለመወጣት በአንድነትና በቁርጠኝነት መነሳሳት አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም አዲሱን ዓመት ስናከብር የተጎዱና የተቸገሩ፣ ኑሮ የከበዳቸውን ድሆች፤ ህመምተኞችን፤ አረጋውያንን ሁሉ በማሰብና ካለን በማካፈል በዓሉን የጋራ ማድረግ እንደሚገባ አስታውቀዋል።

በጋዜጣዋ አዘጋጆች

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review