”የሕዳሴው ግድብ ጥቁሮች እንደምንችል እና እንደምናሳካ ያሳየንበት ታላቅ ስራ ነው”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
ክረምት የመብረቅና የነጎድጓድ ድምፅ በብዛት የሚሰማበት፤ የባሕርና የወንዞች ሙላት የሚያይልበት፤ ሰማይ ደመናን እንደ ጋቢ ተከናንቦ ፀሐይን የሚጋርድበት ወቅት ነው፡፡ ሀገርም አንዳንዴ ዘመኗ እንዳይገለጥ እንደ መብረቅና ነጎድጓድ የሚያጉረመርሙባት፣ የትንሳኤዋ ብርሃን እንዳይታይ ጉምና ጭጋግ ሆነው የሚጋርዱባት ብዙዎች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያዊው የቀለም ሰው ክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል የብዙዎቻችን ትዝታ በሆነው “የዓመቱ ወራት” በተሰኘ የግጥም ስራቸው፤
ሐምሌም ተከተለ ገባ ዝናብ ጭኖ፣
ቀንና ሌሊቱን በዝናብ ጨፍኖ፤ እንዳሉት ኢትዮጵያ ቀንና ሌሊቷ ተጨፍኖ ብዙ ክረምቶችን አሳልፋለች። ርሃብ፣ ጦርነት እና ስንፍናን የመሳሰሉ ክረምቶች በኢትየጵያ ምድር የትንሳኤዋን ብርሃን ጋርደው ለዘመናት አልፈዋል፡፡ አሁንም የቀለም ሰው ከበደ ሚካኤል፤
“አምስት አምስት ቀን ሦስቱን ዓመታት፣
በአራተኛው አንዴ ስድስት ቀን ያላት፣
መሸጋገሪያዋ የጳጉሜን ወር ናት፡፡”እንዳሉት የዘመንን ግርዶሽ የገለጠ፣ አዲስ የብርሃን ዘመንን ያበሰረ ፀሐይ ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሰማይ የጉባ ተራሮችን መሐል ለመሐል ሰንጥቆ ወጥቷል፡፡ ከብርሃን በላይ የሆነው ይህ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ብዙ የሀገር ግርዶሽን የገለጠ እንደሆነም ምሁራን በመመስከር ላይ ናቸው፡፡
ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉት የስነ ልቦና ባለሙያው ማህደር ሳልህ እንዲህ ይላሉ፡፡ የህዳሴው ግድብ ‘አይቻልምና አይችሉምን’ ከወዳጅም ከጠላትም ልቦና ከነ ሥሩ ነቅሎ የጣለ ነው፡፡”
በእርግጥ የዐባይ ወንዝ ገናና ነው። ጋራውን፣ ቋጥኙን እየገነደሰ፣ ሜዳ ሸንተረሩን እየደረመሰ፣ እንዳሻው የሚከንፍ ክንደ ብርቱ ነው፡፡ ከእርሱ ብርታት በላይ ግን “አትንኩት” የሚሉም ብዙዎች ነበሩ፡፡ “ብነካህ ተቆጡ አንቀጠቀጣቸው” እንዳለች ድምፃዊት እጅጋየሁ ሽባባው፡፡
ግን ደግሞ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንዲሉ የዐባይ ጉልበት የብዙ ወንዞች ህብረት ድምር ውጤት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንም እንደ ድር ተጋምደውና ተዛምደው እንደ ንብም አብረው እና ታትረው ከዐባይ ጋር የድል አድራጊነት ቃል ኪዳን አሰሩ፡፡ የሀገርን ማር በጉባ ሰማይ ስር ሰሩ፡፡ ይህ ማር የሀገርን ብዙ መራር ነገሮች የሚያጣፍጥ ነው፡፡
ለአብነትም ድህነት መራር ነው፤ የሚሉት የስነ ልቦና ባለሙያው በድህነታችን ቀዳዳ ታሪካዊ ጠላቶቻችን እየገቡ እርስ በእርስ አናክሰውናል፣ በስንፍናችን ላይ ሌሎች ሸክሞችን ጨምረውብናል፡፡ ወደ ስልጣኔ ጎዳና እንዳንሻገር እንቅፋት ሆነውብናል፡፡
በተለይ ደግሞ የዐባይን ወንዝ አልምተን በፍትሐዊነት እንዳንጠቀም በተለያዩ መልኮች የደረሰብን በደል ከፍተኛ ነው። በመሆኑም የህዳሴው ግድብ ትርጉሙ ከብርሃን በላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ህዳሴ አብሳሪ የንጋት ኮከብ።
በእርግጥም ስንፍናችንን የሚረታ ጉልበት፣ መተባበራችንን የሚያፀና መሰረት፣ ከፍታችንን የሚያሳይ ማማ፣ እንደ ክረምት የጋረደንን ጭጋግ ገፍፎ የሚጥል አዲስ ዘመንን አብሳሪ ፀሐይ ነው የህዳሴው ግድብ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የህዳሴው ግድብን መመረቅ አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክትም እኛ ኢትዮጵያዊያን ታሪክ ሰምተናል፣ አይተናል እንዲሁም ተምረናል፤ ዛሬ ግን ታሪክ ሰርተን ታሪክ ላይ ቆመን ለማውራት በቅተናል ብለዋል፡፡
ህዳሴ የትላንት ቁጭት ማሰሪያ የዛሬን ንጋት ማብሰሪያ መሆኑን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መጪው ጊዜ የኢትዮጵያውያን ጨለማ መገፈፉን ማረጋገጫም ጭምር ነው ብለዋል። ህዳሴ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጥቁር ህዝቦች በሙሉ ታሪክ ሆኖ የሚኖር ታላቅ ገድል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዜጎች ለመጪው ጊዜ የኢትዮጵያን ማንሰራራት በሚያስቀጥሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ ለመሳተፍ እንዲዘጋጁም ጥሪ አቅርበዋል።
ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉት በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሙሉጌታ አስፋው በበኩላቸው፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የከፍታ ዘመን የሚያሳይ ታላቅ ድል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ በጣም ከፍተኛ የሆነውን ድል ያሳካች ሀገር ናት፡፡ በመሆኑም ሌሎች ድሎችን በከፍተኛ ብቃት እንደምታሳካ የህዳሴው ግድብ ቋሚ ምስክር ነው ብለዋል፡፡
ለአብነትም ያደጉ ሀገራት በታላላቅ መድረኮች ይጠቅመናል ብለው ያሰቡትን አጀንዳ በሌሎች ላይ የሚጭኑበት ምስጢር አንዱና ዋናው የኢኮኖሚ አቅም መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ የኢኮኖሚ አቅሟ፣ ዲፕሎማሲ አቅሟ፣ የተመራጭነት አቅሟ በብዙ መልኩ ይጨምራል፡፡ ይህም የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ከፍታ የሚያፀና ነው፡፡ በመሆኑም የህዳሴው ግድብ ከብርሃን በላይ የሆነ የሀገርን የከፍታ ዘመን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በሕዳሴ ግድብ ታሪክ ሰርተን ታሪክ ላይ ቆመን ለማውራት በቅተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ህዳሴ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ህዝቦች ታሪክ ሆኖ የሚኖር ነው ሲሉ አክለዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የትናንት ቁጭት ማሰሪያ የመጪው ንጋት ማብሰሪያ መሆኑን አንስተው፣ ባለፉት አምስት ዓመታት 74 ትሪሊዮን ሊትር ውሃ መያዝ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያን ጥልቅ ጨለማ፣ ከጥልቅ እንቅልፍ ያነቃ በመሆኑ የተያዘው ውሃ ንጋት መባሉን አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ ብልጽግና እና ልክ አይቀሬ መሆኑን ጠቁመው፣ ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች፤ ኢትዮጵያ ተረጂነቷ አብቅቶ ረጂ ሀገር እንደምትሆንም በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ታላቁን የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በደማቸው፣ በላባቸው፣ በገንዘባቸውና በጉልበታቸው በቁጭት የገነቡት የጋራ አሻራቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የታሪካችን እጥፋት ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ ይህ ታሪክ ከእንግዲህ ወደ ኋላ የማይመለስ እና የማይበረዝ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ዳግማዊ ዐድዋ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አክለውም፤ ስንተባበር እና በጋራ ስንቆም እንዲህ አይነት የታሪክ እጥፋትን በታሪካችን ውስጥ እንጽፋለን ብለዋል፡፡ የህዳሴ ግድብ በ14 ዓመታት ጉዞው በርካታ ችግሮች አጋጥመውት የነበረ ሲሆን፣ በእልህና በቁጭት በአይበገሬነት፣ በኢትዮጵያዊያን ላብ፣ ደም፣ ሀብት፣ ገንዘብ፣ ዕውቀትና የሃሳብ አመንጪነት በእንችላለን መንፈስ የተገነባ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ከቆምን እንችላለን፤ ደግሞም ችለን አሣይተናል ያሉት ከንቲባዋ፣ ለዚህም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህያው ምስክር ነው፡፡ ህዳሴን ገነባን ብለን ልንቆም አይገባም፤ ይቻላልን ታጥቀን ከፊታችን ያለውን የብልፅግና ጉዞ ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ እስክትበለጽግ ድረስ በቁጭትና በእልህ እጅ ለእጅ ታያይዘን መጓዝ አለብንም ብለዋል፡፡
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሙሉጌታ አስፋው በበኩላቸው፣ የህዳሴው ግድብ ስኬት፣ ከጥንት እስከ ትላንት በሚታይም ሆነ በማይታይ መልኩ ኢትዮጵያውያንን በመከፋፈል፣ በማጋጨት እና ጥቅሟን አሳጥቶ ልማት ላይ እንዳታተኩር በማድረግ ሲያሴሩባት የነበሩ ኃይሎችን ቅስም የሚሰብር እና ዳግም በክፉ እንዳይመለከቷት ትምህርት የሚሰጥ፣ በአንፃሩ ደግሞ ሀገር ከዘመናት ቀንበር ተላቅቃ በዓለም አደባባይ ቀና ብላ የምትጓዝበትን ዕድልና አቅም የሚፈጥር ድል ነው የሚል ሀሳብ ሰጥተውናል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የታላቁ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት እንዲህ አሉ፡፡ ታላቁ የህዳሴ ግድብ፤ የፅናታችን፣ የላባችን፣ የደማችን፣ የጥረታችን ውጤት፣ የዘመናት ቁጭታችን መደምደሚያ፣ የብልፅግናችን መሰረት፣ የአይበገሬነታችን ምልክት ነው፡፡ በርግጥም የሕዳሴው ግድብ የዘመንን ግርዶሽ የገለጠ፣ የኢትዮጵያን ብልፅግና አይቀሬነት ያሳየ የማይጠልቅ ፀሐይ ነው፡፡
በመለሰ ተሰጋ
#GERD
#Development
#Ethiopia