ብርሃኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር) የማህበራዊ ሳይንስ ተመራማሪ
ሀገራዊ ገዥ ትርክት መገንባት ለሀገር ግንባታ ሂደቱ እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ተጠቁሟል
የሰላም፣ የጤና፣ የደስታ ይሁን
መጪው አዲስ ዓመት አዲሱ ዘመን
እድገት፣ ብልፅግና ይዞ ይምጣልን… እያለ ድምፃዊ አስፋው ፅጌ ዘመን በማይሽረው፣ የአዲስ ዓመት መምጣትን በሚያስናፍቀውና በሚያበስረው ተወዳጅ ዘፈኑ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የእድገትና የብልፅግና ዓመት እንዲሆን ያዜማል፡፡
አዎ! አዲስ ዓመት ትልቅ ትርጉም ያለው ክብረ በዓል ነው፡፡ የራሷ የዘመን አቆጣጠር ቀመር ላላት ኢትዮጵያ ተስፋ የመሰነቂያ፣ የመታደስ መነሻ ምልክት ነው፡፡ በአዲስ ዓመት ሰዎች ባለፈው ዓመት ከሰሩት ለመማር፣ ያላሳኩትን ለማሳካት ጠንክረው እና ታጥቀው የሚነሱበት፣ ጥሩ ያልሆነ ስራ ሰርተው ከሆነ ተፀፅተው መልካም ለመስራት፣ ከተጣሉት ጋር ለመታረቅ፣ የበደሉትን ለመካስ ቃል የሚገቡበትም ጭምር ነው፡፡ ከትናንት የተሻለ ስኬት፣ እድገት፣ ሰላምና ብልፅግና እንዲመጣም ይመኛሉ፤ ያቅዳሉ፤ ይነሳሳሉ፡፡
ይህ በግለሰብ ብቻም ሳይሆን በቤተሰብ፣ በማህበረሰብና በሀገር ደረጃም የሚንፀባረቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ የሰው ዘር መገኛ፣ ረጅም የመንግስትነት ታሪክና የጥንታዊ ስልጣኔ ቀንዲል፣ ቅኝ ያለመገዛት የነፃነት ታሪክ፣ በተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሙዚየምነት፣ በልዩ የዘመን አቆጣጠር ቀመር እና በሌሎች መገለጫዎች ትታወቃለች፡፡
በሌላ በኩል አሁንም ጠንካራ፣ አስተማማኝ ሰላም የተረጋገጠባት፣ ቀጣይነት ያለው እድገት የምታስመዘግብ ሀገርን እውን የማድረግ ትልም ብዙ ስራ የሚጠይቅ ሆኖ ይገኛል፡፡ በታሪክ፣ በሀገራዊ ምልክቶችና ጀግኖች፣ በመንግስት አስተዳደር ስርዓት እንዲሁም በነገ መዳረሻዋ ዙሪያ በተለያዩ ሊሂቃን፣ በማህበረሰቡም ጭምር የጋራ የሆነ መግባባትና አረዳድ አይታይም፤ ልዩነቶች የሚቃረኑ ትርክቶች እንደሚንፀባረቁ ምሁራን ሲናገሩ ይሰማል፡፡
የአዲስ ትልም ጅማሮ በሆነው አዲስ ዓመት ኢትዮጵያ ከግጭት በመውጣት ወደ መግባባት፣ እርቅ፣ ዘላቂ ሰላም፣ እድገትና ብልፅግና የሚወስዳትን መንገድ ትሻለች፡፡ ለዚህ ደግሞ አንደኛው መፍትሔ ኢትዮጵያውያንን የሚያሰባስብ የጋራ ትርክት መፍጠር እንደሆነ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ምሁራን በተለያዩ ጊዜያት አንስተዋል፡፡
ለመሆኑ ትርክት ምንድን ነው?
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ በሶሺዮሎጂ
የትምህርት ዘርፍ በመምህርነትና
ተመራማሪነት፣ ኢንተርናሽናል ሊቭስቶክ
ሪሰርች ኢንስቲትዩትን ጨምሮ
በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት
በተመራማሪነትና አማካሪነት የሰሩት እና “ብሔር-ተኝነት” የተሰኘ መፅሐፍ የፃፉት ብርሃኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር) ለዝግጅት ክፍላችን እንዳብራሩት፣ ትርክት በማህበረሰቡ ተቀባይነት ያገኙ ታሪካዊና ነባራዊ ክስተቶችን፣ ቁሳዊና ኢ-ቁሳዊ ትሩፋቶችንና እሴቶችን እንዲሁም የወል ማንነቶችን የሚገልፅ ንግርት ነው፡፡ ሀገር በመገንባትና በማፍረስም ትልቅ ሚና ያለው ጉዳይ ነው፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት “የትርክት ዕዳና በረከት” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንዳሰፈሩት፣ ትርክት ሆን ተብሎም ይሁን በተለምዶ በዓላማ የሚዘጋጅ ንግርት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ታሪክን፣ እምነትን፣ ባህልንና አመለካከትን ይይዛል፡፡ ትርክት ለበጎ ዓላማ ከተዘጋጀ በአንድ ሀገር ህዝቦች መካከል መግባባትንና አንድነትን ይፈጥራል፡፡ በተቃራኒው ለእኩይ ዓላማ ከሆነ ደግሞ መቃቃር በመፍጠር የግጭት አዙሪት ውስጥ ያስገባል፡፡
ሀገራት የዜጎች ስምምነትና የጋራ ትርክት ውጤት ናቸው፡፡ የጋራ ትርክት የገነቡ ሀገራት የሀገረ መንግስት ግንባታቸውን አጠናቅቀው፤ ብቁ ተቋማትን በመገንባት ዘላቂነት ያለው ሰላምና ብልፅግናን ማረጋገጥ ችለዋል። በኢትዮጵያ የጋራ ስምምነት ላይ የተመሰረተ የታሪክ አረዳድና ትርክት መፈጠር አለመቻሉ ለሀገር ግንባታ ፈተና እንደሆነ በዘርፉ ጥናትና ምርምር ያደረጉ ሰዎች ይናገራሉ፡፡
የማህበራዊ ሳይንስ ተመራማሪው ብርሃኑ (ዶ/ር) እንደሚናገሩት፣ በኢትዮጵያ የሚራመዱ የሚቃረኑ ትርክቶች የሀገር ሰላምና የህዝቦች አንድነት ላይ ፈተና እየደቀኑ መጥተዋል። እሳቸው እንደሚያስቀምጡት፣ በአሁኑ ወቅት “ፍፁማዊ አንድነት” እና “ፍፁማዊ ልዩነት” ትርክቶች” በስፋት ይቀነቀናሉ። የፍጹማዊ አንድነት ትርክት ለብዝሃነት እውቅና የማይሰጥ በመሆኑ በሀገሪቱ ለበርካታ የማንነት ግጭቶች መንስኤ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከዚያ በተቃራኒ የፍፁማዊ ልዩነት ትርክት ደግሞ የጋራ የሆኑ እሴቶችንና ማንነቶችን በመካድና በህዝብ መካከል ጥርጣሬ በመፍጠር ሀገራዊ አንድነት እንዲዳከም አድርጓል፡፡
“የፍፁም አንድነት ትርክት” አቀንቃኞች አንድነቱን ማጠናከርና ማስቀጠል እና ኢትዮጵያን የማትከፋፈል ማድረግ ላይ ትኩረት አድርጎ ከመስራት አልፈው ይሄን የማይቀበሉትን ሁሉ በሀይልም ጭምር ወደ ማጥፋት የሚሄድ አካሄድ ይከተላሉ፡፡ በተቃራኒ የፍፁም ልዩነት ትርክት የሚያቀነቅኑ አካላት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ራሳቸውን ማስተዳደር ከማለት አልፈው ምንም የሚጋሩት ነገር የለም የሚል ትርክት እንዳላቸው ያነሳሉ።
ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረትም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ሀሳብ አላቸው፡፡ በመጽሐፋቸው ላይ እንዳሰፈሩትም፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ በዋናነት “አንድ ዓይነትነት” እና “ፍፁም ልዩነት” የሚባሉ ሁለት ዓይነት ትርክቶች ይራመዳሉ፡፡ “አንድ ዓይነት ነን” የሚል ትርክት የሚያራምዱት እኛን ምሰሉ ሲሉ፤ “ፈፅሞ እንለያያለን” የሚሉት ከሌሎች ጋር የሚያገናኘን አንዳችም ነገር የለም በማለት ይተርካሉ፡፡
“ለአንድ ወገን ዓላማ የተቀረፀ፣ ልዩነትንና ብዝሃነትን ያልተቀበለ፣ ማግባባትና ማቀራረብ ዓላማው ያልሆነ፣ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን የማይፈጥር ትርክት ባለፉት ዘመናት ኢትዮጵያን ፈትኗታል፡፡ ብዙ ዋጋ አስከፍሏታል፡፡” ይላሉ፡፡
ብርሃኑም (ዶ/ር) ይህንን ሀሳብ ያጠናክራሉ፡፡ በኢትዮጵያ የጋራ ታሪክ፣ አረዳድና ትርክት አለመገንባቱ ሀገሪቷን ወደፊት እንዳትራመድ አድርጓታል፡፡ ይህ እያስከተለ ያለውን ችግር ለመቅረፍ በምሁራን ስምምነት የሚፃፍ ሀገራዊ ታሪክ እንዲሁም ሀገራዊ ገዥ ትርክት መገንባት ለሀገር ግንባታ ሂደቱ እጅግ አስፈላጊ እርምጃ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
የጋራ ትርክት እርሾዎችና ቀጣይ ስራዎች
ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሀገር ናት። እያንዳንዳቸው የራሳቸው ቋንቋ፣ ባህል፣ ወግ እንዲሁም ትርክት አላቸው። ይህም ኢትዮጵያ የብዝሃ ትርክት ባለቤት ሀገር እንዳደረጋት የማህበራዊ ሳይንስ ተመራማሪ ብርሃኑ (ዶ/ር) ያነሳሉ። ለአብነት ንግስተ ሳባ ወደ እስራኤል ካደረገችው ጉዞ ጀምሮ በተለያዩ የታሪክና የኃይማኖት መጽሐፍት የተጻፉ፣ የአክሱም፣ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ስልጣኔዎች፣ በኦሮሞ የገዳ ስርዓትና ሌሎች ትርክቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
የብዝሃ ትርክት ባለቤት መሆን በራሱ ጥሩ ቢሆንም የጋራ ትርክት ካልተገነባ፣ ሁሉም በተናጠል ልዩነትን ብቻ ካቀነቀነ እንደ ሀገር አብሮ ለመቀጠል አደጋች ይሆናል፡፡ ከዚህ አንፃር የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ባህል እና ኃይማኖትን የሚገልፁ የተለያዩ ትርክቶች እንዳሉ ሆኖ እንደሀገር የጋራ የሆነ ትርክት መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ብዝሃነት በሚንፀባረቅበት ሀገር ላይ ሁሉም ራሱን የሚያይበት የጋራ ትርክት መገንባት ለሀገር ቀጣይነት፣ ሀብቶቻችንን በጋራ በመጠቀም የምንመኘውን እድገትና ብልፅግናን ለማምጣት አስፈላጊ ነው፡፡
ለምሳሌ፡- አዲስ ዓመት ሲመጣ ኢትዮጵያውያን አዲስ ተስፋ፣ ሰላም፣ እድገት፣ መልካም ነገር ይዞ እንደሚመጣ ያምናሉ፡፡ ይህ ሰዎች አዲስ ዓመትን የሚረዱበት መንገድ ራሱን የቻለ ትርክት አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡ በአዲስ ዓመት ሰዎች ጥሩ ምኞት፣ ተስፋ እንዲኖራቸው፣ ምኞትና ተስፋቸው ወደ ተግባር እንዲለወጥ የሚያደርግ ትርክት አለ፡፡ ተስፋ መሰነቅና አዲስ ዕቅድ መያዝ እንደጥሩ ትርክት የሚታይ እንደሆነ ብርሃኑ (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡
“አንዳንድ የፖለቲካ ሊሂቃን ‘ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚጋሩት ምንም ነገር የለም’ እያሉ ሲያነሱ ይደመጣል፡፡ ይህ ትክክል አይደለም” የሚሉት ብርሃኑ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች በደጉም ሆነ በክፉ ረጅም ዘመናት አብረው ሲኖሩ በጋራ የሰሯቸው አኩሪ እንዲሁም የሰቆቃና የችግር ታሪኮች እንዳሉ ያነሳሉ። ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ለመውረር ከውጭ የሚመጣን ሀይል በመከላከል የጋራ የሆነ ሥነ ልቦና አዳብረዋል፡፡ ለምሳሌ፡- በዓድዋ ጦርነት በአንድነት በመቆም ቅኝ ሊገዛ የመጣውን የጣሊያን ወራሪ በማሸነፍ ነፃነታቸውን አስጠብቀው ዘልቀዋል፡፡ ከዚህ አኳያ የዓድዋ ድልን በተመለከተ የሚነገሩና የሚፃፉ ነገሮች፣ ድሉን ለማጉላት የዓድዋ ድል መታሰቢያን በመገንባት የተሰሩ ስራዎች የጋራ ትርክት ግንባታ አካል ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ዳር ድንበሯ የታወቀ፣ ሉዓላዊነቷ የተረጋገጠ ኢትዮጵያ በምትባል አንዲት ሀገር የሚኖሩ፣ ዕጣ ፈንታቸው የተሳሰረ፣ አብሮ የማደግ፣ የመበልፀግ፣ ሰላም የማግኘት፣ የመከበር ፍላጎት ያላቸው ህዝቦች መኖራቸው ለጋራ ትርክት ግንባታ መነሻ መሆን ይችላል፡፡ ይህንን ምኞት፣ ተስፋ፣ ፍላጎትና መሻት ወደ ተግባር መቀየር የሚያስችል ነገር በጋራ ለመገንባት መስራት እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሌላው ለጋራ ትርክት ግንባታ መሰረት የሚሆን የአሁኑ ትውልድ አሻራ እንደሆነ ብርሃኑ (ዶ/ር) ያነሳሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን የዓባይ ውሃና ሌሎችን ሀብቶች በማልማትና በመጠበቅ የጋራ የሆነ አረዳድና አተያይ አላቸው፡፡ በከተማ ልማት በተለይ በኮሪደር ልማት እየተሰሩ ያሉና ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ልማቶች ለጋራ ትርክት ግንባታ ጠቀሜታ አላቸው። ሁሉም ‘የእኔ’ ብሎ የሚወስዳቸው ነገሮች እየበዙ ሲሄዱ የጋራ ትርክት እየተፈጠረ ይሄዳል፡፡ ልማት እየሰፋ፤ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ‘ከዚህ እጠቀማለሁ’፤ ‘የእኔ ነው’ የሚለው እምነት እያደገ ሲሄድ በዚያው ልክ የጋራ የሆነ ትርክትም እየተፈጠረ ይመጣል፡፡
ኢትዮጵያ ትልቅ የህዝብ ቁጥር፣ ግዙፍ ኢኮኖሚ የምታንቀሳቅስና ከባህር በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ ሀገር ሆና የባህር በር አልባ ሆና መቆየቷ ኢትዮጵያውያንን ሲያንገበግብ የቆየ ጉዳይ እንደሆነ የሚያስታውሱት የማህበራዊ ሳይንስ ተመራማሪው ብርሃኑ (ዶ/ር)፣ በቅርብ ጊዜ ጉዳዩን አጀንዳ በማድረግ በተሰራው ስራ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆን እንዳለባት ከሞላ ጎደል በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ እምነት እየተያዘበት መጥቷል፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ ‘የባህር በር ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፤ እኔ እንደ አንድ ዜጋ የሚጠበቅብኝን ለመወጣት ዝግጁ ነኝ’ የሚል እምነት ማሳደር ሲጀምር ስለባህር በር የሚኖረው ትርክት የጋራ ይሆናል፡፡
ብርሃኑ (ዶ/ር) እንደሚገልፁት፤ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታትም ለሀገር አንድነትና አብሮነት የጋራ ትርክት መገንባት አስፈላጊ እንደሆነ በመገናኛ ብዙሃንና በተለያዩ መድረኮች ለማስረፅ የተሄደበት ርቀት እንደ ጥሩ ይወሰዳል። ኢትዮጵያ ውስጥ ብዝሃነት እንዳለ ሁሉ የጋራ የሆነ፣ ሁላችንንም በአንድነት የሚይዝ ትርክት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡
ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በመፅሐፋቸው እንዳሰፈሩት፣ ኢትዮጵያ ህብረ ብሔራዊነት የሚታይበት ሀገር እንደመሆኗ የሚገነባውም ትርክት ህብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክር የጋራ ትርክት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም የመደመር እሳቤ መፍትሔ ይሆናል፡፡ የመደመር እሳቤ ብዝሃነትን የሚያስተናግድና አንድነትን የሚያጠናክር ትርክት የያዘ ነው፡፡
“የጋራ ትርክት መፍጠር ያልተቻለው ብሔራዊ መግባባት ባለመፈጠሩ ነው” የሚሉት ብርሃኑ (ዶ/ር)፣ ከዚህ አኳያ በመጀመሪያ ብሔራዊ መግባባት ለማምጣት የተጀመረው የሀገራዊ ምክክር ሂደት ውጤታማ እንዲሆን መደገፍ ያስፈልጋል፡፡ ሀገራዊ ትርክት የሚቀረፀው በሀገራዊ መግባባት ነው። የሀገራዊ ምክክር ሂደት የመጨረሻው ውጤት የጋራ መገለጫዎችና ምልክቶች እንዲሁም ተያይዞ የሚመጣ ሀገራዊ የጋራ ትርክት መፍጠር ነው፡፡ ብሔራዊ መግባባት ከተፈጠረ በኋላ መግባባት በተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ የሚፈጠሩ ትርክቶች በሙሉ የጋራ ትርክት እየሆኑ ይሄዳሉ፡፡
በዚህ ሂደትም ምሁራን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳዎችን በማቅረብ፣ በማዳበር፣ በጥናትና ምርምር መፍትሔዎችን በመጠቆም ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ የሲቪክ ማህበራት፣ የኃይማኖትና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሀሳብ በማዋጣት፣ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን እና ስምምነት የተደረሰበት ጉዳይ ተግባራዊ እንዲሆን የራሱን ሚና መወጣት እንዳለበት ብርሃኑ (ዶ/ር) ጠቁመዋል፡፡
በጥቅሉ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያውያንን የሚያስተሳስሩ የጋራ ማንነቶችን ለመገንባት አበረታች ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ የተደበቁ ሀገራዊ ሀብቶችንና ታሪኮችን በማውጣት ለጋራ ሀገር ጥቅም እንዲውሉ፣ ትውልዱ እንዲማርባቸው በማድረግ ለአብነት እንደ አንድነትና እንጦጦ ፓርኮች፣ ወዳጅነት አደባባይ፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ ብሔራዊ ቤተ መንግስትን በማደስ የተሰሩ ስራዎችን መጠቀስ ይቻላል፡፡ በመጪው አዲስ ዓመትም ብሔራዊ መግባባትን ለማምጣት የተጀመረውን የሀገራዊ ምክክር ሂደት፣ የባህር በር የባለቤትነት ጥያቄና ሌሎችንም ውጤታማ በማድረግ የጋራ ትርክት ግንባታውን ማጠናከር ይገባል እንላለን፡፡
በስንታየሁ ምትኩ