አዲስ አበባ ከአዲሱ ዓመት ጋር በስልጣኔ አድማስ ስር እንደ ንጋት ኮከብ አዲስ ሆና ብቅ ብላለች
የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ፣
ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ
ማን ያውቃል? እንዳለ ባለቅኔው መንግሥቱ ለማ፤ እኔም እንደመስቀል ወፍ እያየኋት ተናፋቂ ስለሆነችው ከተማ እያብሰለሰልኩ ነው፡፡ እናም ዛሬ እግሬና ልቤ ሽክፍ ብለውልኛል፡፡
ያለሁበት የፒያሳ አካባቢ አንድ ስም ግን ብዙ ታሪክና ትዝታን ያዘለ ድንቅ ስፍራ ነው፡፡ እናም ከዐድዋ ድል መታሰቢያ የኢትዮጵያውያን ታሪክ እየመነጨ እንደ ዐባይ ፏፏቴ በቸርችር ጎዳና ሲለው በአራት ኪሎ ብቻ ወዳሻው አቅጣጫ ውበትን እንደ ጋቢ ተከናንቦ ሲነጉድ በዐይነ ልቦናዬ ይታየኛል፡፡
እንዲህ እንደ እኔ በተመስጦ ከተመለከቱት በትዝታ ፈረስ አዝማናትን ሽምጥ እያስጋለበ ትናንትን የሚያስመለክት፤ ደግሞም በተስፋ ሰረገላ ወደፊት እያስፈነጠረ ጭው ባለ በርሃ ድንገት ፈሰስ እንደምትል ካፊያ ቀልብን በሀሴት የሚያረሰርስ ስፍራ ነው፤ፒያሳ፡፡
ታዲያ የያኔው ስልጣኔዋ እንደተጠበቀ ሆኖ የትናንቷ ፒያሳ እንደ አደይ አበባ የፈካ የሰው ፍቅር እንጂ በዘመናዊነት ምልከታ ያን ያህል ልብ የሚያሞቅ ውበት አላት ለማለት አያስደፍርም ነበር፡፡
ቢሆንም ይህ እኔ የቆምኩበት ስፍራ አራዳ፤ ፒያሳ የአዲስ አበባ የውበትም ሆነ የስልጣኔ እምብርት ስለመሆኑ አያሌ ፀሐፍት መስክረውለታል፡፡ አዎ! አራዳ በሀገራችን ብዙ የመጀመሪያ የሚባሉ ነገሮች የተጀመሩበት ስፍራ ነው። እንዲያውም በብዙዎች ዘንድ አራዳ ማለት ዘመናዊነትን የሚከተል እንደሆነም ይነገራል፡፡
በትክክልም ፒያሳ፣ እነ ሜሪ አርምዴ፣ እነ አስናቀች ወርቁ፣ እነ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር. . . ጥበብን ከዘመናዊነት ጋር የተቋደሱበት “ዘጠኟን ዓለም” አስር ያደረጉበት ስፍራ ነው። ለዚህም የውቤ በርሃ ትዝታ አሊያም የስብሃትን “ሌቱም አይነጋልኝ” መፅሐፍ ምስክሬ ነው፡፡
በመጋቢት 1965 ዓ.ም የታተመችው መነን መፅሔት ደግሞ በ40ዎቹ እና በ50ዎቹ ዘመናዊ ሙዚቃ፣ ፉሽን እና የምሽት ህይወት አዲስ አበባ ውስጥ በተለይ አራዳ አካባቢ አብቧል፤ ትለናለች። ደግሞም ከዚህ ጋር ተያይዞ ስማቸው በዋናነት ይጠቀሱ ከነበሩት መካከል ሜሪ አርምዴ አንዷ ነበረች። እነ ሜሪ አርምዴ ዘመናዊ ዳንስን እና የሴቶችን የፀጉር ቤት…..የጀመሩበት….ያስተማሩበት …..ስፍራ ነው አራዳ፤ ፒያሳ፡፡
ደራሲ ስብሃት ገብረእግዚአብሄር “ትኩሳት” ብሎ በጠራው መጽሐፉ ጀርባ፣ ፒያሳ ሂድ፤ ፒያሳ ወደ ሕይወት ትመልስሃለች” እንዳለው፡፡ ደራሲ መሐመድ ሰልማን ደግሞ “ፒያሳ ማህሙድ ጋ ጠብቂኝ በተሰኘ ድንቅ ድርሰቱ የፒያሳን ውበት እንደ ጅረት እያፈሰሰ፣ እንደ ወንዝ እያገማሸረ አስኮምኩመናል፡፡
ፒያሳ አንድ ሺህ አንድ መቶ ካፌዎች ያሉባት ቅመም የሆነች ሰፈር ናት፡፡ አንድ ሺህ አንድ መቶ ቆንጆ ልጃገረዶች ደግሞ በካፌዎቿ ውስጥ ተኮልኩለው ኮካ በ‘ስትሮ’ ይጠጣሉ፡፡ ‘ስትሮ’ ምን እንደሆነ ካላወቅክ የፒያሳ ልጅ አይደለህም ማለት ነው፡፡ ‘ስትሮ’ በቆንጆ ልጅ ከንፈርና በቆንጆ ብርጭቆ መሀል የተሰራ የላስቲክ ድልድይ ነው፤ እያለ ፒያሳን አንቆለጳብሷታል፡፡ በርግጥ ይህ በዘመኑ እውነት ነው፡፡ ይሁን እንጂ አዲስ አበባ የትናንት ውበቷ በዘመን ጉም ተሸፍኖ ዘመንን እገፋ በመንጎዱ ብዙዎቹን ማስቆጨቱ “ስሟ አዲስ እሷ አሮጌ” የመባሉ ነገር የአዘቦት ተረክ ሆኖ መቅረቱም የማይካድ ሀቅ ነበር፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የአዲስ አበባ ፀሐይ ደመናውን ገፍፋ የታሪካችን እምብርት በሆነው በዓድዋ ድል መታሰቢያ በኩል አድርጋ ዳግም በፒያሳ ላይ ወጥታለች፡፡ ፒያሳም እንደ አዲስ ተወልዳለች፡፡ እንደ መስከረም ሰማይ አዲስ ውበትን ተጎናፅፋ ቀንም ሌሊትም ደምቃ ትታያለች፡፡
አዲስ አበባ በኮሪደር ልማት አያሌ ውብ የሕይወት ሰበዞቿ እየተሰፉ በብዙ ጌጦችም እንድትዋብ ሆናለች፡፡ በፒያሳ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ተዘዋውሬ እንደተመለከትኩት ከተማዋ በቅርብ ዓመታት ውስጥ አሮጌ መልኳን እንደ ንስር አድሳ፣ አዲስ ግርማና ሞገስን ተላብሳለች፡፡ አዲስም፣ አበባም ሆናለች። እነ እሪ በከንቱ፣ እነ ካዛንቺስ፣ እነ ዶሮ ማነቂያ፣ እነ ተረት ሰፈርን፣ እነ ሽሮሜዳን የመሳሰሉ አካባቢዎች የትናንት ጎስቋላ መልካቸው እንደ ደመና ተገፍፎ አዲስ ግርማ ሞገስን ተላብሷል፡፡
እነዚያ ጭንቅንቅ ያሉ መንገዶች፣ ጣሪያቸው ያረጀ፣ ማገራቸው የላላ፣ ምሶሷቸው ያዘመመ እና ባለ ላስቲክ ግድግዳዎቹ የደቀቁ ስፍራዎች በውብ መናፈሻዎች፣ በሰፋፊ መንገዶች እና በሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች እየተተኩ ነው። በርግጥም አዲስ አበባ ገና ከጫጉላ ቤት እንደወጡ ሙሽሮች፣ እንደ ቀይ ሐር ፈትል፣ በለምለም መስክ ላይ እንደሚቦርቁ እንቦሶች እና እንደ ተከፈለ ሮማን ዐይንንም ልብንም እየማረከች ነው፡፡
እናም አዲስ አበባ በዕድሜ መግፋት የተጫጫናትን አዚም እንደንስር አራግፋ፤ እንደ መስቀል ወፍ ውብ ገፅታን ተላብሳ እያየናት የምትናፈቅ ከተማ ሆናለች። ከአዲሱ ዓመት ጋር በስልጣኔ አድማስ ስር እንደ ንጋት ኮከብ አዲስ ሆና ብቅ ብላለች፡፡
ጋሽ ጥላሁን ገሰሰ (የክብር ዶክተር) “በመዋደድ ጉዞ ዳገት በፍቅር መንገድ ላይ. . . እየተሳሳቁ ዳግም እያዩ መናፈቅ” እንዳለው አዲስ አበባ እያየናት ተለወጠች፤ አብረናት እየኖርንም ተናፋቂ ሆነች። በርግጥ በዓለማችን እንዳሉ ማራኪ ከተሞች አዲስ አበባን እንደ ስሟ መለወጥ ‘ይቻላል!’ የሚል መንፈስን ማምጣትና በዚያው ልክ ችሎ ማሳየት ውስብስብ እና ዘርፈ ብዙ ስራን የሚጠይቅ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ግን በራስ አቅም ይህን ማድረግ ተችሏል፡፡
በዓለማችን በርካታ ሀገራት የ‘አይቻልም’ን ክፉ መንፈስ በመስበር በይቻላል በመተካት ሁለንተናዊ ለውጥ አምጥተዋል፡፡ ለአብነትም ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያና የጀርመን ከተሞችን ተሞክሮዎች ማንሳት እንደሚቻል የዓለም ባንክ መረጃ ያመለክታል፡፡
የእነዚህ ሀገራት የቀደመ ታሪካቸው ሲገለጥ ያላደጉ ተደርገው የሚቆጠሩ ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ውርጅብኝ በጥረታቸው ማገገም ችላለች፡፡ ተስፋ መቁረጥን በብሩህ ተስፋ፣ አይቻልምን በይቻላል ለውጠዋል።
እውቁ ዴንማርካዊው አርክቴክት እና የከተማ ዲዛይን አማካሪ ጃን ጌል “Cities for People” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መፅሐፍ መሰረት የከተሞች ልማትና ገጽታ በአምስቱ የሰው ልጅ ህዋሳት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት፡፡ ከተሞች ለዐይን የሚማርኩ፣ ለጆሮ የሚጥሙ፣ የሚዳሰሱ፣ መዓዛቸው መንፈስን የሚገዛ፣ ጣዕማቸው የሚጣፍጥ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ከተሞች በዕድገታቸው ውስጥ ነዋሪዎቻቸውን፣ ትናንትን፣ ዛሬን እና ነገን ታሳቢ ሲያደርጉ ከሞት ወደ ሕይወት ይሸጋገራሉ፡፡
አዲስ አበባም እርጅና ተጫጭኗት ባለችበት ወቅት ልክ ከሞት ወደ ሕይወት ምዕራፍ የመሸጋገርን ያክል፣ አሊያም ጭልጥ ብለን ከሄድንበት የእንቅልፍ ዓለም እንደመንቃት አይነት የተደራረበባትን የዘመናት ሸክም አራግፋ በአዲስ የለውጥ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፡፡ አበባነቷን፤ አዲስነቷን እያስመሰከረች፡፡
በተለይም ከተማዋ በኮሪደር ልማቱ አዲስ የውበት ሸማን ተጎናፅፋለች። አዲስ ድምቀት፤ አዲስ ፍካት፣ አዲስ ግርማ ሞገስን ተላብሳለች፡፡ ፅዱ ጎዳናዎች፣ ማራኪ የመናፈሻ ስፍራዎች፣ እንደ መንትዮች አንዱን ካንዱ በውበት ማበላለጥ የሚያስቸግሩ አስደማሚ ሕንፃዎች ከተፈጥሮ ጋር የሚያስታርቁ ልዩ ልዩ የአረንጓዴ ስፍራዎች በመዲናዋ የቀደመ ውበት ላይ ወዝና ለዛን ጨምረው ምድረ ገነት አድርገዋታል፡፡ እናም አዲስ አበባ እንደ መስቀል ወፍ አብራን እያለች ተወዳጅና ተናፋቂ ሆናለች፡፡
በመለሰ ተሰጋ
#Holiday
#Addisababa
#Ethiopia