ትውልድ ተሻጋሪ የመዝናኛ ስፍራዎች

You are currently viewing ትውልድ ተሻጋሪ የመዝናኛ ስፍራዎች

ደማቅ የመንገድ መብራቶች የራሳቸውን ፀሐይ ፈጥረው ምሽቱን ብርሃን አላብሰውታል፡፡ ከሚያማምሩ የመንገድ መብራቶች ስር፣ ከውብ የእግረኛ ጎዳናዎች አጠገብ በልዩ ጭፈራና ቀለም የታጀበው የውሃው ፋውንቴን ተጨማሪ ድምቀት ሆኗል፡፡ ልጆችም በደስታ ወዲያ ወዲህ ይሯሯጣሉ፡፡ ያንን ድንቅ ቅፅበት ሰዎች በስልካቸው ቀርጸው ለማስቀረት ጥረት ያደርጋሉ። ካሜራ ባለሙያዎችም የጓደኛሞችን፣ የፍቅረኛሞችንና የቤተሰቦችን ታሪክ በሌንስ ይቀርጻሉ። ሰዓቱ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል ቢሆንም አራት ኪሎ ፕላዛ አካባቢ ያለው ድባብ ግን የቀን ይመስላል።

አዲስ አበባ አራት ኪሎን ጨምሮ በፒያሳ፣ በካዛንቺስ፣ በእንጦጦ፣ በወዳጅነት አደባባይ፣ በአንድነት ፓርክና በሌሎችም አካባቢዎች የገነባቻቸው አዳዲስ የመዝናኛ ስፍራዎች ለከተማዋ ሌላ ውበት እና እሴት ጨምረውላታል፡፡ እነዚህ ቦታዎች ነዋሪዎች አዲሱን ዓመት (እንቁጣጣሽ) ጨምሮ በመስከረም ወር የሚከበሩ በዓላትን ከቤተሰብና ጓደኞቻቸው ጋር ጥሩ ጊዜ እንዲያሳልፉ ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል፡፡ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን ቀልብ በመሳብ የገቢ ምንጭም እየሆኑ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የመናፈሻዎች እና መዝናኛ ስፍራዎች መበራከት ለበርካቶች የስራ እድል ሲፈጥሩ ለነዋሪዎችና ለጎብኚዎች የመዝናኛ አማራጭ ሆነዋል፡፡ ብዙ ጊዜ  ለመዝናናት ከቤት ለማይወጡ ወይም መዝናናት ሲባል ከአዲስ አበባ መውጣት እንደሆነ ለሚያስቡ ሰዎችም መዲናዋ ያከናወነቻቸውና እያከናወነቻቸው የሚገኙት ፕሮጀክቶች ትልቅ እድል የሚፈጥሩ ናቸው፡፡

አዳዲሶች የመዝናኛ አማራጮች ለመዝናናት ጥሩ አጋጣሚ ከፈጠረላቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ሃና ብርሃነ መስቀል አንዷ ናቸው። ወይዘሮ ሃና እንደሚሉት፣ ባለፈው ዓመት ልጆቼን ወደ እንጦጦ እና አንድነት ፓርኮች እንዲሁም ወዳጅነት አደባባይ ፓርክ ወስጄ ነበር። በእነዚህ ቦታዎች ተደስተውና ተዝናንተው ነው የተመለሱት፡፡ ከዚህ በፊት ከተማዋ ‘ህንጻ ብቻ ሆነች፤ የመዝናኛ አማራጭ ያስፈልጋል’ የሚል ጥያቄ ነበራቸው። አሁን ግን በከተማዋ ውስጥ የተሰሩት መናፈሻዎች ተፈጥሮንና ባህልን ለልጆች የሚያስተምሩ ናቸው፡፡ ለእሳቸውም ጭምር ከስራ በኋላ እና በእረፍት ቀናት አማራጭ የመዝናኛ ቦታዎች ሆነውላቸዋል፡፡

አክለውም “በአዲሱ የ2018 ዓመትም በቴሌቭዥን ያየናቸውን ሌሎች አዳዲስ መናፈሻዎችንና የውሃ ፋውንቴኖችን የማየትና የመዝናናት ሃሳቡ አለን። አዲስ አበባ ለአዳዲስ ፓርኮችና መዝናኛ ስፍራዎች ግንባታ እየሰጠችው ያለው ትኩረት የሚደነቅ ነው። በአዲሱ ዓመትም ሌላ አዲስ ነገር ይኖራል ብዬ እገምታለሁ። እነዚህን ስፍራዎች መጠበቅ እና መንከባከብ፣ ሳያቆሽሹ መጠቀም ደግሞ የሁላችንም ኃላፊነት ነው” ሲሉም አክለዋል።

በእርግጥም አዲስ አበባ ያደሰቻቸው ነባር ቅርሶችና የገነባቻቸው አዳዲስ ፕሮጀክቶች ለመዲናዋ ነዋሪዎች ትልቅ የመዝናኛ አማራጭ ከመሆናቸውም ባሻገር የኢትዮጵያን ገጽታ ለአለም የሚመሰክሩ፣ ከቱሪዝም ዘርፍም ከፍተኛ ገቢ ለማግኘት የሚያስችሉ መሆናቸውን በርካቶች ይናገራሉ፡፡

ወይዘሮ ሶስና ሙሉጌታ በአስጎብኚነት ሙያ ከ15 ዓመታት በላይ ሰርተዋል፡፡፡ ላለፉት 7 ዓመታት ደግሞ ኩታ አስጎብኝ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የተባለ ድርጅት በመመስረት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ወይዘሮዋ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት ማብራሪያ፣ “አዲስ አበባን ጨምሮ በአራቱም አቅጣጫ ኢትዮጵያን ከጎበኘሁ በኋላ እኔ ያወኩት ‘የሀገራችን የቱሪዝም ሃብት ለሀገር ውስጥ ጎብኚዎችና ለውጭ ቱሪስቶች መተዋወቅ አለበት’ በሚል ቁጭት ነው ወደዚህ ስራ የገባሁት” ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያ ለቱሪዝም መዳረሻ የሚሆን በርካታ ሃብቶች አሏት፡፡ ሀገራችን ሁሉም ነገር አንድ ላይ የተሰጣት ነች፡፡ ከራስ ዳሽን እስከ ዳሉል በተፈጥሮ ተዘርዝረው የማያልቁ ባህላዊ ሃብቶች እና ዘመናትን ያስቆጠሩ የሃይማኖት እና ቅርስ ታሪኮች እንዲሁም በርካታ አዳዲስ እና ነባር መዳረሻዎች እንዳሏት የገለጹት ወይዘሮዋ፣ “እኛም በመዲናችን ከሚገኙ አለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ጋር በመተባበር ነባርና አዳዲስ የመዝናኛ መዳረሻዎችን የማስጎብኘትና ልጆችን ከአካባቢያቸውና ከተፈጥሮ ጋር የማስተዋወቅ ስራ እየሰራን ነው፤ በአዲሱ ዓመት ደግሞ በርካታ ስራዎችን የመስራት እቅድ አለን” ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ባለሙያዋ እንደሚሉት፣ አዳዲስ መዳረሻዎችን መስራት እና እድሳት የሚያስፈልጋቸውን ቅርሶች ማደስ ለአንድ ሀገር ቱሪዝም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ቅርሶች እንክብካቤ እና እድሳት ይፈልጋሉ፡፡ በአዲስ አበባ ነባር መዳረሻዎችን በማደስና አዳዲስ የመዝናኛ እና የቱሪዝም መዳረሻዎችን በመጨመር እየተሰራ ያለው ስራ የሚደነቅ ነው። ምክንያቱም በመዲናችን የተሰሩት ፕሮጀክቶች ከዓመታት በፊት ሲጠየቁ የነበሩ ጥያቄዎችን የመለሱ ናቸው፡፡

“ከዚህ ቀደም ወደ አዲስ አበባ ለኮንፈረንስ የሚመጡ ሰዎችን አንድ ቀን አራዝማችሁ ከተማዋን ጎብኙ ለማለት አስቸጋሪ ነበር፡፡ ጎብኝዎችም ‘እንደ ሌሎች ሀገራት መዝናኛዎችና ፓርኮች እንኳን የሏችሁም’ ይሉን ነበር” በማለት በስራ ላይ ጎብኚዎች የነገሯቸውን አጋጣሚ  የሚጠቅሱት ወይዘሮ ሶስና፤ በአዲስ አበባ የተሰሩት አዳዲስ የመዝናኛ መዳረሻዎች ይህን ጥያቄ  የመለሱ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ቱሪዝሙን የሚያግዙ በርካታ የመሰረተ ልማት ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ የተሰሩት እንደ አስጎብኚ ሲጠየቁ የነበሩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ወይዘሮ ሶስና፣ “በመዲናችን የብሔራዊ ሙዚየም መታደሱ የሚያስደስት ነገር ነው፡፡ እኛም ይህን እና መሰል መስህቦችን ለጎብኚዎች በዲጂታል ሚዲያና በተለያዩ አማራጮች እያስተዋወቅን ነው፡፡ በአዲሱ ዓመትም አጠናክረን እናስቀጥለዋለን” በማለትም አስረድተዋል፡፡

የማርገብ ቱር ኤንድ ትራቭል ስራ አስኪያጅ ማቴዎስ እሸቴ ከዚህ ቀደም በጉዳዩ ላይ ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት፣ “በአዲስ አበባ ቱሪስቶችን ለመሳብ እና ለማቆየት የሚያስችሉ በርካታ ተጨማሪ ስራዎች መሰራታቸው ለቱሪዝም ውጤታማነት ትልቅ አበርከቶ አለው” ብለዋል፡፡

ስራ አስኪያጁ በገለጻቸው፣ “ከዚህ በፊት ወደ ሀገር የምናመጣቸው ወይም የምናስጎበኛቸው ቱሪስቶች አብዛኛውን ጊዜ አዲስ አበባ ገብተው ነበር የሚወጡት፡፡ አሁን ግን በከተማዋ የተሰሩ ሙዚየሞችና ፓርኮች እንዲሁም ጎዳናዎችን እናስጎበኛቸዋለን፡፡ አዲስ ፕሮጀክት ሲመረቅ የጉብኝት ዝርዝራችን ውስጥ በማካተት ቱሪስቶችን ለማቆየት እና ከተማዋንም ራሳችንንም ለመጥቀም የሚያስችሉ ስራዎችን እንሰራለን” ብለዋል፡፡

አዲስ አበባ የቱሪስት መዳረሻነቷን የበለጠ ለማጠናከር በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ ትገኛለች፡፡ ይህንን ጉዳይ በውል እንረዳለን የሚሉት አቶ ማቴዎስ፣ “በመዲናዋ የተሰሩትን አዳዲስ ፕሮጀክቶች በአግባቡ በማወቅ እና ለጎብኚዎች በማስተዋወቅ በኩል የሚጠበቅብንን ኃላፊነት እየተወጣን ነው” ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ለዚህ ማሳያ ሲጠቅሱም፣ ቱሪስቶች ከዚህ በፊት አዲስ አበባ ውስጥ ብዙ አይቆዩም ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ ቆዩ ከተባለም አንድ እና ሁለት ቀን ብቻ ነበር፡፡ ምክንያቱም ከተማዋ እንዳሁኑ ምሽት ላይ ብርሃናማ አልነበረችም፡፡ መንገዶቿ ለእግር ጉዞ አይመቹም ነበር፡፡ እንደ እንጦጦ እና አንድነት ፓርክ የመሳሰሉት መናፈሻዎች ብዙ አልነበሩም፡፡ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ገና አልተሰራም ነበር። ስለዚህ ቱሪስቶች አዲስ አበባን እንደ መሸጋገሪያ ብቻ ነበር የሚጠቀሙባት፡፡ አሁን ግን ይህ ነባራዊ ሁኔታ ተቀይሯል። አዲስ አበባ ራሷ የሚዝናኑባትና የሚጎበኟት ከተማ ሆናለች በማለት ነው፡፡

አዲሱ ዓመት በመዲናችን አዲስ አበባና በተለያዩ የሀገራችን ከፍሎች የተለያዩ በዓላት የሚከበሩበት ወቅት ነው፡፡ መስቀል ደመራ እና ኢሬቻ በከፍተኛ ድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በአዲሱ ዓመት በዓሉን ለማክበር ከተለያዩ የኢትዮጵያ እና የዓለም አካባቢዎች ወደ መዲናዋ የሚመጡ የህብረተሰብ ክፍሎችና የውጭ ሀገራት ቱሪስቶች እንጦጦ እና አንድነት ፓርኮችን፣ ዓድዋ ድል መታሰቢያን፣ አራት ኪሎ ፕላዛን ጨምሮ ሌሎች አዳዲስ የቱሪዝም ቦታዎችና መዝናኛ ስፍራዎችን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። በዚህ ሂደት ደግሞ የአስጎብኚዎች ሚና ትልቅ ነው፡፡

እንደ ወይዘሮ ሶስና ገለጻ፣ አዲስ አበባ ላይ ያለው ነገር በጥሩ ሁኔታ ተሰርቷል። የሚታደሱትም ቆንጆ ሆነው ታድሰዋል። እንቁጣጣሽ፣ መስቀልና ኢሬቻን ለማክበር ወደ መዲናዋ የሚመጡ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች እነዚህን አዳዲስ የመዝናኛ ስፍራዎች ይጎበኛሉ፡፡

“አስጎብኚዎች ሀገራዊ ጨዋነትና ባህሉን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀት አለብን፡፡ እኛ እንደ ኩታ አስጎብኚ ለአዲሱ ዓመት በሁሉም መስክ ዝግጅት አድርገናል፡፡ ከወዲሁ የማስተዋወቅ ስራ እንሰራለን” ሲሉም ገልጸዋል፡፡

አዲሱ ዓመት ያለንን የምናስተዋውቅበትና የምናጎላበት ብሩህ ጊዜ እንደሚሆን እምነታቸውን የገለጹት ወይዘሮ ሶስና፣ “መንግስት ለአስጎብኚ ድርጅቶች የሚችለውን ሁሉ ድጋፍ ማድረግ አለበት፡፡ እያንዳንዱ ዜጋም በተሰማራበት ዘርፍ ለሀገሩ ዘብ የመቆም፣ ነባርና አዳዲስ የመዝናኛ መዳረሻዎችን የማስተዋወቅ ኃላፊነት አለበት” ሲሉም በማጠቃለያ ሃሳባቸው አንስተዋል፡፡

በጊዜው አማረ 

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review