አፍሪካ ወደ ከባቢ አየር በካይ ጋዞችን በመልቀቅ አራት በመቶ ብቻ ድርሻ እንዳላት የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም በገፀ ድሩ ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡ በካይ ጋዞችን በመልቀቅ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሀገሮች ናቸው፡፡ በተመሳሳይ በቀድሞው የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን (በአሁኑ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን እና የደን ልማት መስሪያ ቤት) በ2014 ዓ.ም “የተሻሻለው በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ዕቅድ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሰነድ እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት ያላት ድርሻ ዝቅተኛ ነው፤ ዜሮ ነጥብ ዜሮ አራት በመቶ ይገመታል፡፡
አፍሪካም ሆነ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ያላቸው ድርሻ አነስተኛ ቢሆንም በከፍተኛ ደረጃ በትሩ እያረፈባቸው ይገኛል፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ ህልውና ላይ ከፍተኛ አደጋ ከደቀኑ ፈተናዎች አንዱ እንደሆነ በዓለም አቀፍ የሳይንስ ማህበረሰብና በፖለቲከኞች ዘንድ መግባባት ተደርሶበታል፡፡ ለአደጋው መፍትሔ መስጠት ካልተቻለ፣ የባህር ወለል መጠን መጨመር፣ ረሃብ፣ ድርቅ እንዲሁም የዓለምን አንድ ሶስተኛ የሚሆነውን የእፅዋትና እንስሳት ዝርያዎች ማጣትን ጨምሮ አሰቃቂ ውጤቶች ሊያስከትል እንደሚችል መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2024 ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ተለዋዋጭ የሆነ የአየር ፀባይና የአየር ንብረት ለውጥ በመላው አፍሪካ ረሀብን፣ የደህንነት ዋስትናን ማጣት፣ ስደትን በማባባስ በሁሉም የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳረፈ ይገኛል፡፡ ባለፉት ዓመታትም በአፍሪካ በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ ሙቀት ተመዝግቧል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት “Climate change takes increasingly extreme toll on African countries” በሚል ርዕስ በፈረንጆቹ 2025 በገፀ-ድሩ ያወጣው ጽሑፍ እንደሚያሳየው፤ ባለፈው ጥቅምት ወር በደቡብ ሱዳን ባጋጠመ ጎርፍ 300 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል። ይህ አሃዝ 13 ሚሊዮን የህዝብ ቁጥር ባላት ሀገር ከፍተኛ ከመሆኑ ባሻገር ደካማ የመሰረተ ልማት አቅርቦትና ግጭት ችግሩን ውስብስብ እንዲሆን አድርጎታል።
በኢትዮጵያ ደን ልማት የሰው ሰራሽ ደን ምርምር ዳይሬክተር አባይነህ ደረሮ (ዶ/ር) ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሙቀት መጨመርን ተከትሎ እያጋጠመ ባለው የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ በአፍሪካ በተደጋጋሚ ጊዜ የድርቅና ጎርፍ አደጋዎች እያጋጠሙ፣ ህይወት ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳረፉ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያም በቅርብ ዓመታት በቦረና፣ በምስራቅ እና ሰሜን አካባቢዎች ባጋጠመው ድርቅ በእንስሳት ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ ከዚህ ባሻገር እንዲህ ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎች የሚያጋጥሙበት ጊዜ እያጠረ መጥቷል። በዚህም ምክንያት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ፈተና ሆኗል፡፡ ምክንያቱም አብዛኛው የግብርና ስራ በዝናብ ላይ ተመስርቶ የሚከናወን ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ከፍተኛ ዝናብ ሲኖር ወንዞች እየሞሉ በሰውና ኢኮኖሚ ላይ ውድመት እያደረሱ ነው፡፡ ይህም ዜጎችን ለስደትና ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየዳረገ ይገኛል፡፡
በቀድሞው በኢፌዴሪ የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን በ2014 ዓ.ም የተዘጋጀ ሰነድ እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያ በካይ ጋዝን ወደ ከባቢ በመልቀቅ ያላት ድርሻ ዝቅተኛ ቢሆንም የችግሩ ገፈት ቀማሽ ከሆኑ ሀገራት አንዷ ናት፡፡ በፈረንጆች አቆጣጠር ከ1952 ወዲህ በኢትዮጵያ የሙቀት መጠን በአማካይ በአንድ ድግሪ ሴልሺየስ መጨመሩን ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ከባለፉት አስርት ዓመት ወዲህ እንደ ድርቅና ጎርፍ የመሳሰሉ የአየር ንብረት ለውጥ አስከፊ ክስተቶች በተደጋጋሚ መመልከትም የተለመደ ሆኗል፡፡
በጉባኤው የተወደሰው የኢትዮጵያ እርምጃ
ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ከጷጉሜን 3 እስከ ጳጉሜን 5 ቀን 2017 ዓ.ም የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችና ባለሙያዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡ ጉባኤውን ኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ህብረት በጋራ በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን ከ25 ሺህ በላይ ሰዎች ተሳትፈውበታል፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “እዚህ የተገናኘነው በህልውናችን ላይ ለመደራደር አይደለም፤ የመጪውን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተስማማ የዓለም ኢኮኖሚ ዲዛይን ለማድረግ ነው፡፡ ትክክለኛውን መንገድ ከመረጥን ስነ ምህዳሯን ሳታጠፋ ወደ ኢንዱስትሪ መሸጋገር የቻለች አህጉርን እውን ማድረግ እንችላለን፡፡” ብለዋል፡፡
ግልጽ ዓላማ በማስቀመጥና በቁርጠኝነት በመስራት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የሚስማማ ኢኮኖሚ መገንባት እንደሚቻል ኢትዮጵያ ማሳያ ናት፡፡ ትልቅ ርዕይ በመያዝ ህብረተሰቡን በማሳተፍ መስራት ከተቻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ያሳዩ ተነሳሽነቶች ተግባራዊ መደረጋቸውን አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በ2011 ዓ.ም በጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ባለፉት ሰባት ዓመታት ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል ችላለች። በዚህም ሙቀትን በመቆጣጠር፣ የአፈር መሸርሸርን በመከላከል፣ የተፋሰሶችን ስነ ምህዳር በመጠበቅ፣ ምግብ፣ የስራ ዕድል ፈጠራ ምንጭ እንዲሁም የወጭ ንግድን በማሳደግ እምርታ ማምጣቷን አብራርተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ሳይንስ ትምህርት ክፍል የስነ ምህዳር ተመራማሪው ተሾመ ሶሮምሳ (ፕሮፌሰር) ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፣ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመከላከል በተለይ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በመጀመር ያከናወነችው ተግባር በተምሳሌነት የሚወሰድ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታትም በርካታ ችግኞችን በመትከል የካርበን ዳይኦክሳይድ ልቀትን በመቀነስ፣ የዝናብ መጠንና የከርሰ ምድር ውሃ አቅርቦት እንዲጨምር፣ በደን የተሸፈነ የመሬት ሽፋንንና የግብርና ምርታማነት በማሳደግና በሌሎች ዘርፎች ውጤት ማምጣት ተችሏል፡፡
ሌላው ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን አሉታዊ ተፅዕኖዎች ለመግታት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የሚስማሙ የሌማት ትሩፋት ፕሮግራምና በመስኖ ስንዴን የማልማት ስራ ተግብራለች። በዚህም የምግብ ስርዓትን ማሻሻል፣ ከውጭ የሚገባውን ምግብ በመቀነስ የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥ በምታደርገው ጥረት ስኬት አምጥታለች።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታየውን የምግብና የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ችግሮች ለመፍታት አፍሪካዊ መፍትሔዎች መኖራቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ለዚህም ራስን የመቻል፣ የአንድነትና የታዳሽ ሀይል ልማት አፍሪካዊ ምልክት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማሳያ እንደሚሆን አንስተዋል፡፡ የስነ ምህዳር ተመራማሪው ተሾመ (ፕ/ር) እንደሚሉት፣ የህዳሴ ግድብ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመቋቋም ከፍተኛ ጥቅም ያለው ልማት ነው፡፡ ግድቡ ሀይል ከማመንጨት ባለፈ ከዕፅዋት በበለጠ በትነት መልክ ዝናብ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም በግድቡ አካባቢ ሰፊ የሆነ የአካባቢ ጥበቃና የችግኝ ተከላ በመከናወኑ የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተፅዕኖን በመከላከል ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣል፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን በተለይ በገጠሩ አካባቢ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሀይል ፍጆታ በማገዶ እንጨት ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ ግድቡ በርካታ ኢትዮጵያውያንን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማስቻል የደን ጭፍጨፋ ያስቀራል፡፡ የኤሌክትሪክ ሀይሉ ከታዳሽ ሀይል አማራጭ የሚመነጭ ሲሆን ከኢትዮጵያ ባለፈ የጎረቤት ሀገር ዜጎችንም ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል ከወሰደቻቸው እርምጃዎች ሌላኛው ንፁህና ኢነርጂ ቆጣቢ የምግብ ማብሰያን ተደራሽነት ማሳደግ ነው፡፡ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በ2016 ዓ.ም በገፀ-ድሩ ያወጣው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ በኢትዮጵያ ከ90 በመቶ በላይ ለምግብ ማብሰያነት ጥቅም ላይ የሚውለው የእንጨት ማገዶ ደንን በመጨፍጨፍ የሚገኝ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ብሔራዊ የንፁህ ማብሰያ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት በማገዶ እንጨት በጭስ እየታፈኑ ምግባቸውን የሚያበስሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቤተሰቦች በተለይ ሴቶችን ከጫና ለማላቀቅ እየሰራች እንደሆነ በንግግራቸው አንስተዋል፡፡
በከተሞች እየተተገበረ ባለው አረንጓዴና አካታች የሆነ የስማርት ሲቲ ንቅናቄም የእግረኛ እና የሳይክል መንገዶች በመስራትና በማስፋት እንዲሁም አረንጓዴ፣ ምቹና ደህንነታቸው የተጠበቁ የህዝብ መዝናኛ ስፍራዎችን ተደራሽ በማድረግ እየሰራች ትገኛለች፡፡ በነዳጅ የሚሰሩ የትራንስፖርት ዓይነቶችን ባለማበረታታትና በመቀነስ የጋዝ ልቀትን በመቀነስ ጤናማ የሆኑ ከተሞችን ለመፍጠር እየተጋች ነው፡፡
አባይነህ (ዶ/ር) እንዳብራሩት፣ በኢትዮጵያ በፈረንጆች አቆጣጠር በ2011 ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ከተነደፈ በኋላ የደን ሽፋንን በመጨመር፣ የትራንስፖርት፣ የሀይልና የተለያዩ ዘርፎች ከበካይ ጋዝ ልቀት የፀዱ እንዲሆን የተለያዩ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ለምሳሌ፡- በግብርናው ዘርፍ የአረንጓዴ አሻራ እና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ተቋቁሟል። በዚህም በየዓመቱ ከሀገር ውስጥ ገቢ ምንጭ ከሚመደበው ዓመታዊ በጀት ውስጥ ከዜሮ ነጥብ አምስት እስከ አንድ በመቶ ያህሉ ለአካባቢ ጥበቃ ስራ እንዲውል የሚመደብ ሲሆን፣ ይህም ለዘርፉ የሚያስፈልገውን ሀብት በማሰባሰብ አካባቢን በተሻለ ለመጠበቅ ያግዛል፡፡ በደን የሚሸፈነውን መሬት በማሳደግ፣ ማህበረሰቡ ደኑን እየጠበቀ ተጠቃሚ እንዲሆንና በዚህም የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ደን ሽፋን እንዲጨምር በከተማና ገጠር እየተሰራ ነው፡፡ ካርቦንዳይ ኦክሳይድ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቅበት አንደኛው ምክንያት የአፈር መከላት ነው፡፡ በዚህ ረገድ የአፈር መሸርሸርን ለመከላከል እርከንና የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ህብረተሰቡን በማሳተፍ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡
በሀይል ልማት ዘርፍም ከትናንት በስቲያ የተመረቀው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ፣ ከነፋስ ሀይል በማመንጨት፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን መጠቀምን የሚያበረታቱና የካርቦን ልቀትን በከፍተኛ መጠን የሚቀንሱ ጠንካራ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ያነሱት አባይነህ (ዶ/ር)፣ ይህም ሀገሪቱ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ ትልቅ ቦታ የሚያሰጣት ነው፡፡
የስነ ምህዳር ተመራማሪው ተሾመ (ፕሮፌሰር) እንደሚሉት፣ በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመከላከል የኢትዮጵያን አረንጓዴ አሻራ ሞዴል መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ያላትን የማይናወጥ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው፡፡ ፕሮግራሙ አሳሳቢ ለሆኑት ስነ ምህዳራዊ ፈተናዎች መፍትሔ ከመስጠት ባሻገር በምድር ላይ ህይወት ላላቸው ፍጥረታት ህልውና መቀጠል ወሳኝ ነው፡፡ ከተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከል፣ የብዝሃ ህይወት ጥበቃና ዘላቂ ልማት ግቦች ጋር የሚጣጣም ነው፡፡ ተሾመ (ፕሮፌሰር) ለኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ቀን እውቅና በመስጠት በዓለም የአካባቢ ጥበቃ ቀን ውስጥ ተካትቶ እንዲሰራበት ደብዳቤና የፕሮጀክት ሀሳብ አዘጋጅተው ለድርጅቱ ማቅረባቸውን አንስተው፤ እውቅናው ቢሰጥ ኢትዮጵያ አካባቢን በመጠበቅ እያከናወነች ያለውን ተምሳሌታዊ አመራር የሚያከብር እና ፕላኔታችንን ደህንነቷ ተጠብቆ ለአሁኑና ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ዓለም አቀፋዊ አጋርነት ለመፍጠር ትልቅ መነሻና አቅም እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
አባይነህ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ አፍሪካ በፈረንጆች አቆጣጠር 2063 ሰላማዊና ደህንነቷ፣ ፍትህ የተረጋገጠባት፣ ሁሉን አቀፍ እድገት የሚመዘገብባትና የበለፀገች አህጉርን ለመፍጠር እቅድ ይዛ እየሰራች ትገኛለች፡፡ ኢትዮጵያ እስከታች ድረስ ተቋማትን በመዘርጋትና በማጠናከር፣ ታዳሽ ሀይልን በማሳደግ እንዲሁም ጠንካራ አመራር በመስጠት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የምትሰራቸው ስራዎች ለብዙ የአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት የሚሆኑ ናቸው፡፡
አፍሪካ ሰፊና ሀብታም አህጉር ናት። ኢትዮጵያም በአፍሪካ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ያላት፣ በአፍሪካውያን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ጉልህ ሚና ያላት ሀገር ናት፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተፅዕኖንም በመከላከልና በመቋቋም እያከናወነችው ያለው ስራ ለአፍሪካ መፍትሔ የሚሆን፣ አፍሪካዊያንን ብቻም ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በትብብር መስራትን የሚጠይቅ ነው፡፡
በስንታየሁ ምትኩ
#Africa
#Ethiopia
#Climate Change