አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ መዘዞች ተጋላጭ ብቻ ሳትሆን ለችግሩም የመፍትሄ አካል የመሆን ጅምሯን አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ አሳስበዋል፡፡
በብራዚል በሚካሄደው የዓለም የአየር ንብረት ጉባዔ (ኮፕ 30) ላይ የአፍሪካዊያን አጀንዳ የሚቀርብበት የአዲስ አበባ ዲክላሬሽን በተሳካ ሁኔታ ጸድቋል፡፡
በኢትዮጵያ አስተናጋጅነትና በአፍሪካ ህብረት ትብብር በአዲስ አበባ ከተማ ሲካሄድ የቆየው ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ ተጠናቋል።
የጉባኤውን ማጠቃለያ ቁልፍ መልዕክቶች ያስተላለፉት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ መዘዞች ተጋላጭ ብቻ ሳትሆን ለችግሩም የመፍትሄ አካል የመሆን ጅምሯን አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት አሳስበዋል።
አፍሪካዊያን የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በቁርጠኝነት የሚሰሩበት የ”አዲስ አበባ ድንጋጌ ስምምነት” በጉባዔው ፀድቋል። ይህን ስምምነት ሳይሸራርፉ መተግበር ከአፍሪካ እንደሚጠበቅም ፕሬዚደንቱ አፅንኦት ሰጥተው መልዕክት አስተላልፈዋል።

ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያ በዘርፉ የምታበረክተውን አስተዋፅኦ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል። ለጉባኤው ስኬት አስተዋፅኦ ላበረከቱ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርን ወክለው መልዕክት ያስተላለፉት በአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ፀጥታ ኮሚሽን ኮሚሽነሩ ባንኮሊ አዲዎየ፣ አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄዎች ለማምጣት ትብብርን አጠናክራ ማስቀጠል ይገባታልም ብለዋል።
በኢትዮጵያ አስተናጋጅነትና በአፍሪካ ህብረት ትብብር በአዲስ አበባ ከተማ ሲካሄድ የቆየውን ይህን ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ ኢትዮጵያ በብቃት ማስተናገዷን የጉባኤው ተሳታፊዎችና መሪዎች ገልፀው ምስጋና አቅርበዋል።
ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ “ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማሳለጥ፣ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ” በሚል መሪ ሀሳብ ከጳጉሜን 3 ጀምሮ ሲካሄድ ቆይቷል።
ከዋናው ጉባዔ አስቀድሞ ለተከታታይ ቀናት ቅድመ ጉባዔዎቹ በተሳካ ሁኔታ መካሄዳቸውንና ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦች መነሳታቸው መገለፁ ይታወሳል።
ኢትዮጵያም የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን በጋራ በመከላከል ዙሪያ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ያላትን አቋም እና ያከናወነቻቸውን ተግባራት በጉባኤው አንፀባርቃለች።
በጉባኤው አካባቢያዊ መፍትሄዎችን ከአህጉራዊ የአየር ንብረት ስትራቴጂዎች ጋር ማስተሳሰር በሚቻልበት ሁኔታዎች ላይ ሰፊ ምክክሮች ተደርገዋል። አፍሪካ በአየር ንብረት አስተዳደር ትክክለኛ ቦታ ለመያዝ የምታደርገውን ጥረት የሚያግዙ በርካታ ውሳኔዎችም ተላልፈዋል።
በጉባዔው 25 ሺህ ያህል ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን፤ ከመድረኩ ጎን ለጎንም ከ199 በላይ ውይይቶች መካሄዳቸው ነው የተገለጸው፡፡
43 የሚሆኑ በአየር ንብረት ለውጥ ዘርፉ ላይ የተሰማሩ አልሚዎች በጉባዔው በተካሄደ ኤግዚቢሽን ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡
በይታያል አጥናፉ