የቀድሞው የብራዚል ፕሬዝዳንት መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ አሲረዋል በሚል 27 አመት እስር ተፈረደባቸው

You are currently viewing የቀድሞው የብራዚል ፕሬዝዳንት መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ አሲረዋል በሚል 27 አመት እስር ተፈረደባቸው

AMN – መስከረም 2/2018 ዓ.ም

የብራዚል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቀድሞ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ዣየር ቦልሶናሮ ላይ የ27 አመት የእስር ቅጣት አሳልፏል ።

ፍርድቤቱ በቦልሶናሮ ላይ የፍርድ ውሳኔውን ያሳለፈው አሁናዊው የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ወደ ስልጣን በመጡበት አመት በተደረገው ምርጫ ቢሸነፉም በስልጣን ለመቆየት እና መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ አሲረዋል በሚል የቀረበባቸውን ክስ ተከትሎ ነው።

የቀኝ ዘመሙ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወዳጅ የሆኑት የቀድሞ ፕሬዝዳንት የፍርድ ሂደት ከፍ ያለ ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ቆይቷል።

የትራምፕ አስተዳደር የፍርድ ሂደቱ በነጻነት ሀሳብን የመግለጽ መብትን የተጋፋ እና ፖለቲካዊ ተነሳሽነት ያለው ነው ሲል በዋና ዳኛው ላይ ማዕቀብ መጣሉ ይታወሳል።

ከዚህ ባለፈም ከብራዚል ወደ አሜሪካ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ የ50 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ አድርጓል።

ቦልሶናሮ በበኩላቸው ክሱን ፍጹም ሀሰተኛ በሚል አጣጥለው በ2026ቱ የብራዚል ምርጫ እንዳልሳተፍ የተሸረበብኝ ሴራ ነው ብለዋል።

5 ክሶችን የመሰረተው አቃቤ ህግ በበኩሉ ከመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ባለፈ በፕሬዝዳንት ሉላ ዳሲልቫ እና ምክትላቸው ላይ እንዲሁም በጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ላይ የግድያ ሙከራ በማድረግ ከሷቸዋል።

የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጠበቆች በበኩላቸው የፍርድ ውሳኔው እጅግ የተጋነነ በእርግጥም የፖለቲካ ውሳኔ የተቀላቀለበት ይመስላል ሲሉ ተቃውመዋል ።

ሮይተርስ ይዞት በወጣው ዘገባ በአምስት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች በ70 አመቱ ቦልሶናሮ ላይ የተላለፈው ውሳኔ በሀገሪቱ ታሪክ በቀድሞ ፕሬዚዳንት ላይ ተግባራዊ በመሆን የመጀመሪያው ነው ብሏል።

ውሳኔውን ተከትሎ የ70 ዓመቱ ዣየር ቦልሶናሮ ቀሪ ዘመናቸውን በእስር ቤት ሊያሳልፉ የሚገደዱበት እድል ከፍተኛ መሆኑ ተሰምቷል።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review