ኢትዮጵያዊያኑ የአሜሪካ ጎት ታለንት ተወዳዳሪዎች

You are currently viewing ኢትዮጵያዊያኑ የአሜሪካ ጎት ታለንት ተወዳዳሪዎች

AMN – መስከረም 3/2018 ዓ.ም

የሰርከስ ጠቢባኑ ታምራት እና ቶማስ (TT Boys) በአሜሪካ ጎት ታለንት (AGT) ከፍተኛ አድናቆት በማግኘት ወደ 4ኛው ዙር ዉድድር ያለፉ ኢትዮጵያዊያን የተሰጥኦ ተወዳዳሪዎች ናቸዉ፡፡

ካናዳ በሚገኘው ታላቁ የዓለማችን ሰርከስ ማዕከል፤ ሰርከስ ዲሶሌ ለ10 ዓመታት በኮንትራት የሰሩ ሲሆን በታዋቂዉ የእግር ኳስ ተጫዋች ሊዮኔል ሜሲ የሕይወት ታሪክ ውስጥ የተሰጣቸውን የሰርከስ ሚና በብቃት ተወጥተዋል።

ወጣቶቹ ኢትዮጵያ ሰፊ የፈጠራ ክህሎትና እምቅ ተሰጥኦ እንዳላትም በአለም መድረክ በማስተዋወቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነ-ጥበብ፣ ሥነ-ጥበብና ፈጠራ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ (ረ/ፕ)፤ በአሜሪካ ጎት ታለንት በከፍተኛ አድናቆት ወደ የሚቀጥለው ዙር ያለፉት የሰርከስ ጠቢባን ታምራት እና ቶማስ ሀገራቸውን በዓለም መድረክ በበጎ ስላስጠሩ ምስጋና ማቅረባቸዉም የሚታወስ ነዉ፡፡

ኢትዮጵያን በመወከል በዉድድሩ ላይ በመሳተፍ ላይ የሚገኙት ታምራት እና ቶማስ፤ 3ኛውን የዉድድር ምዕራፍ በብቃት አጠናቀዉ ወደ 4ኛዉ ዙር ያለፉ ሲሆን አንድ ሚሊዮን ዶላር የሚያስገኘዉን ሽልማት ለመቀዳጀት ብርቱ ፉክክር በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

ተወዳዳሪዎቹ ታዋቂ የአለማችን የአሜሪካ ጎት ታለንት ዳኞች ሳይመን ኮዌልን እና ሃዊ ማንዴልን ጭምር ማስደነቃቸዉም ተነግሯል፡፡

ሳይመን “እናንተ ጀግኖች ናችሁ ድንቅ ብቃት አሳይታችኋል” በማለት አበረታቶአቸዋል፡፡

ሶፊያ ቨርጋራ በበኩሏ “ይህ አስፈሪ ትዕይንት ነዉ፡፡ እናንተ ግን በብቃት ተወጥታችኋል ” በማለት አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡

የመድረክ አስተዋዋቂዉ ሄነሪን ጨምሮ በሺህ የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የሰርከስ ጠቢባኑ ታምራት እና ቶማስ በመጨረሻዉ ዉድድር ላይ የመሳተፍ እድል እንዲያገኙ ጥያቄ ማቅረባቸዉ ተነግሯል፡፡

በዉድድሩ የአሜሪካዊያኑ ድምጽ ትልቅ ድርሻ ያለዉ በመሆኑ በአሜሪካ የሚኖሩ ትዉልደ ኢትዮጵያዊያን ድምጽ በመስጠት የሚሳተፉ ከሆነ ቲቲ ቦይስ ትልቅ ምእራፍ ላይ ይደርሳሉ ተብሎም እየተጠበቀ ነዉ፡፡

ተወዳዳሪዎቹ በ4ኛው ዙር ምን ይጠብቃቸዋል የሚለዉ ጥያቄ ኢትዮጵያዊያንን ብቻ ሳይሆን የአሜሪካ ጎት ታለንት ዳኞችንና ተሳታፊዎችንም ጭምር እያነጋገረ ይገኛል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review