ሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በሚቀጥሉት አምስት አመታት በርካታ አዳዲስ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ወደ አገልግሎት እንደሚያስገባ ተገለፀ

You are currently viewing ሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በሚቀጥሉት አምስት አመታት በርካታ አዳዲስ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ወደ አገልግሎት እንደሚያስገባ ተገለፀ

AMN – መስከረም 3/2018 ዓ.ም

ሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በሚቀጥሉት አምስት አመታት በርካታ አዳዲስ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ወደ አገልግሎት እንደሚያስገባ የግሩፑ ሊቀመንበር ሼህ መሀመድ አላሙዲን ተናገሩ።

የ2017 ዓ.ም የቤተሰብ ቀንን እያከበረ ያለው ግሩፑ የተሻለ አፈጻጻም አስመዝገበዋል ላላቸው አመራሮቹና ሰራተኞቹም እውቅና ሰጥቷል።

በእውቅና መርሀ ግብሩ በበይነ መረብ መልዕክት ያስተላለፉት የግሩፑ ሊቀመንበር ሼህ መሀመድ አላሙዲን ለሰራተኞቻቸው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ አበርክቶ እያደረገ ያለው ግሩፑ በሚቀጥሉት አምስት አመታተትም የስራ እድልን የሚፈጥሩ አዳዲስ ሜጋ ፕሮጀክቶች ወደ ስራ እንደሚገቡ አብስረዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ መመረቅ እንዳስደሰታቸው የገለጹት ሊቀመንበሩ ለሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕም ተጨማሪ አቅም ይፈጥርልናል ብለዋል።

መመረቁን በጉጉት ሲጠብቅ ለነበረው የኢትዮጵያ ህዝብም እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ በበኩላቸው 2017 የተሻለ ውጤት ያስመዘገብንበት ነው ብለዋል።

ሀገርን የጠቀሙ እና ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን የሰራንበት አመት ነው ያሉት ስራ አስፈጻሚው፤ በአበባ፣ በቡና እና ሻይ ምርት ወደ ውጪ በመላክ 263 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አስገኝተናል ሲሉ ተናግረዋል።

በያዝነው አመትም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ በጎ አበርክቶ ያላቸው ፕሮጀክቶች ወደ አገልግሎት ይገባሉ ነው ያሉት።

የድንጋይ ከሰል፣ የመድሃኒት ፋብሪካ እና ኢትዮጵያን የሚመጥን ዘመናዊ ሆስፒታል በያዝነው አመት የሚመረቁ መሆናቸውንም አቶ ጀማል ተናግረዋል።

ግሩፑ የማህበራዊ ሀላፊነቱን ለመወጣት በ2017 ዓ.ም 1.1 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉም ተመላክቷል።

በፍቃዱ መለሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review