ህዳሴ አይችሉም ባዮችን ያሳፈረ ነው ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ

You are currently viewing ህዳሴ አይችሉም ባዮችን ያሳፈረ ነው ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ

AMN – መስከረም 4/2018 ዓ.ም

ህዳሴ አይችሉም ባዮችን ያሳፈረ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅን በማስመልከት የመዲናዋ ነዋሪዎች የድጋፍ ሰልፍ አካሂደዋል።

በድጋፍ ሰልፍ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የህዳሴ ግድብ የጂኦ ፖለቲካ ብያኔን የለወጠ፣ የዲፕሎማሲን ኢፍትሃዊ አተያይ የቀየረ፣ ለመላው ጥቁር ህዝቦች የማንሰራራት ድልን ያበሰረ፣ አይችሉም ባዮችን ያሳፈረና ያስደመመ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ግድቡ ኢትዮጵያ መቻሏን በተግባር ያሳየ፣ በዓለም መድረክ በመገናኛ ብዙሀንና መሪዎች መነጋገሪያ በመሆን የአይበገሬነት ተምሳሌት ሆኖ የተጠቀሰ የአንድነታችንና የጋራ አሻራችን፣ የማንደራደርበት ዘላለማዊ ሀውልታችን ሆኖ ተገንብቷል ብለዋል።

የከተማው ነዋሪው ከማለዳው አንስቶ በድል አድራጊነት በነቂስ መውጣቱ የድልና የታሪክ እጥፋት ባለቤት መሆኑን ያመላክታል ሲሉም አክለዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ፣ ግድብ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ከሀሳብ አመንጪነት እስከ ፈፃሚነት ከዳር ለማድረስ ባልተቋረጠ ህዝባዊ ድጋፍ ብሔራዊ ክብርን ለማስጠበቅ የሰሩበት፣ በሲሚንቶና ብረት ብቻ ሳይሆን በላብ፣ በደም፣ በአጥንት የተገነባ የሉአላዊነታችን መሠረት መሆኑ መቼም አይዘነጋም ብለዋል።

ግድቡ ከድህነት በመውጣት በራስ አቅም በመልማት ፍላጎት፣ ትጋት እና ቁርጠኝነት የታገሉ የዚህ ትውልድ ውጤት ነው ብቻም ሳይሆን የዘመኑ ቁጭት ምላሽ በመሆኑ መጪው ትውልድ ይኮራበታል ሲሉ አብራርተዋል።

የኛ ትውልድ ዘካሪ ብቻ ሳይሆን እንደቀደምት አባቶቻችን ታሪክ ሰሪም ጭምር መሆኑን ለዓለም አሳይተንበታል ብለዋል።

ከንቲባዋ በአንድ ልብ ታሪክ በመስራት ለመጪው ትውልድ ምንዳን የምታስረክብ ሀገር የማስቀጠሉ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ከተባበርን፤ በአንድነት ከቆሞን የትኛውም ጫና እንደማያስቆመን ዳግም አስመስክረናል ያሉት ከንቲባዋ፤ ግድቡ እናቶችን ከኩራዝ ጭስ የሚያላቅቅ፣ የኢኮኖሚ ማንሰራሪያ ብቻም ሳይሆን ስትራቴጂያዊ ኩስምና ማብቃያ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ይህንን ህዝባዊ አንድነት በሌሎች የልማት ስራዎች መድገም ይጠበቃል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በሚካኤል ህሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review