የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ “ታላቁ የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ደስታችንን ለመግለጽ በመገናኘታችን እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል።
ከንቲባዋ ይህን ያሉት “በህብረት ችለናል” በሚል መሪ ሀሳብ በመስቀል አደባባይ እየተከናወነ በሚገኝው ህዝባዊ ድጋፍ ላይ ነው። በዚሁ ወቅት ግድቡ ተጀምሮ እስከተጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ በተለያየ ዘርፎች ድጋፍ ላደረጉ ኢትዮጵያውን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ግድቡ ከመምህር ፣ እስከ ሾፌር ፣ ከእንጨት ለቃሚ እስከ ሊስትሮ ሁሉም ከጉያው ቀንሶ እውን ያደረገው የሁሉም ኢትዮጵያውያን ኩራት ምንጭ የሆነ ሀብት ነው ብለዋል።
የለውጡ መንግስት ወደ ስልጣን በመጣበት ጊዜ ግድቡ በውስብስብ ችግሮች ተተብትቦ እንደነበር ያስታወሱት ከንቲባዋ፤ ግድቡ ዛሬ ላይ ለበቃበት ስኬት ይደርስ ዘንድ ግድቡን ከገባበት ቅርቃር ለማውጣት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሰጡት አመራር ምስጋና እንደሚገባው አንስተዋል።

በዛ ፈታኝ በሆነው ሀሩር ወጣትነታቸውን ለኢትዮጵያ ብልጽግና ሰውተው በግድቡ ግንባታ ለተሳተፉ ፣ የግድቡን ደህንነት በመጠበቅ የተሳተፉ የጸጥታ አካላት፣ በአለም አቀፍ መድረክ ስለ ግድቡ ሲከራከሩ የነበሩ አምባሳደሮች ፣ ዲፕሎማቶች እና የዲያስፖራ አባላት በከንቲባዋ ንግግር ተመስግነዋል።
ለግድቡ እውን መሆን ሳይሰስቱ ያላቸውን በሙሉ ለሰጡ እንዲሁም ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላዋጣው የአዲስ አበባ ነዋሪ ከንቲባዋ ምስጋናቸውን አቅርበው ፤ አለም አቀፍ ጫና በበረታበት ጊዜ ለሀገራቸው ድምጽ ለሆኑ የማህበረሰብ አንቂዎች እና የሚዲያ ሰዎችንም አመስግነዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በላባችን በደማችን የገነባነው የወል ስኬታችን ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ “በራሳችን ወጪ በላብ እና የደም ዋጋ ጨምር ገነባነው ፣ ጨረስነው ፣ አስመረቅነው” ሲሉ ደስታቸውን ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈ የግድቡ መጠናቀቅ በቀጣይ ለምንጀምራቸው ፕሮጀክቶች የአንድነት ሀይል ውጤት ምን ያህል ሀያል እንደሆነ አመላክቷል ብለዋል።
በዳዊት በሪሁን