የህዳሴው ግድብ ተገቢውን እውነታ በማስረዳት ለኢትዮጵያ እናቶች ፍትህ እንዲያገኙና ብርሃን እንዲያዩ ማድረግ ችሏል ሲሉ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለት በመስቀል አደባባይ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ መመረቁን አስመልክቶ “በህብረት ችለናል” በሚል መሪ ሀሳብ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፤ የሁላችንም የአዕምሮ፣ የእውቀት፣ የላብ፣ የደም፣ የጉልበትና ሃብት ውጤት የሆነውን የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ መመረቅና በይፋ ወደ ስራ መግባት ለመዘከር ለዚህ ለፍሰሃ ቀን በመብቃታችን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
አክለውም የታላቁ ህዳሴ ግድብ እውነታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያ እናቶችን ችግር በማስረዳት ፍትህ ያገኘንበት የዘመኑ ትውልድ ዘላለማዊ ሀውልት ነው ሲሉ ገልጸውታል።

የህዳሴ ግድብ የድህነትና የርሃብ ገጽታችንን የቀየረ፣ አይችሉም የሚለውን እሳቤ የሰበረ፣ መቻላችንን ያበሰረ የዚህ ትውልድ አሻራ የክብር አደራ ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያውያን ብርቱ ነን ያሉት ፕሬዝዳንት ታዬ፤ እንደ ብርቱ ቋሚ እና ማገር ፣ እንደ ጠንካራ ድር እና ማግ ከተቀናጀ፣ ኢላማውን እና ግቡን ከለየ ኢትዮጵያዊው ይችላል፤ የሚሳነው ነገር አይኖርም ነው ያሉት፡፡
ፕሬዝዳንቱ አክለውም በቀጣይ ለሰላም ለልማትና ለዘላቂ ሀገራዊ ግንባታ ቁርጠኛ በመሆን ክፍተቶችን በማረም ሀገራችንን ወደ ብልጽግና በማሻገር ኃላፊነታችንን እንወጣለን ብለዋል።
ለህዳሴው ግድብ እዚህ መድረስ የዜጎች ተሳትፎ፣ የአመራሩ ጥበብና የዲፕሎማሲው ጉዞ ቁርጠኝነትን የሚጠይቅ አድካሚ የነበረ መሆኑን አውስተው፤ ፍሬው ጣፋጭ፣ ለሀገራችን ህዝቦችና ለአፍሪካውያን ብርሃን የፈነጠቀ ብለውታል።
በአለኸኝ አዘነ