ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመላው ኢትዮጵያውያን የትጋት እና የጽናት ውጤት ነው ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ

You are currently viewing ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመላው ኢትዮጵያውያን የትጋት እና የጽናት ውጤት ነው ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ
  • Post category:ልማት

AMN – መስከረም 5/2018 ዓ/ም

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በስኬት መጠናቀቁን በማስመልከት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመላው ኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት የትጋትና የጽናት ውጤት ነው። ግድቡ ለስኬት የበቃው በርካታ ፈተናዎችን አልፎ መሆኑን ገልጸው፤ ይኸም እውን የሆነው በህዝቡ ድጋፍና በመንግሥት ቁርጠኛ አመራር መሆኑን ተናግረዋል።

ግድቡ ኢትዮጵያውያን በዓባይ ጉዳይ ላይ ከታሪክ ሰሚነት ወደ ታሪክ ሰሪነት የተሸጋገርንበትና በፈተና ውስጥ የተገኘ የትውልድ አሻራ እንደሆነም ገልጸዋል።

የክልሉ ህብረተሰብ ከግድቡ ትሩፋት ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ገልፀው፥ ይህም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እና የብልጽግና ጉዞ ማሳካት የሚያስችል ስኬት ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የመርሃግብሩ ተሳታፊዎች “ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድባችን የዓባይ ዘመን ትውልድ ትክክለኛ ሀሳብ በትክክለኛው ጊዜ የገነባነው ዘመን ተሻጋሪ ቅርስ” እንዲሁም “ሕዳሴ ግድባችን በራሳችን አቅም የገነባነው የአንድነታችንና የአብሮነታችን ምሰሶ” የሚሉና ሌሎች መልዕክቶችን አሰምተዋል።

በመርሃ ግብሩም የአሶሳና አካባቢዋ ነዋሪዎች፣ ከፍተኛ አመራሮች እና የፀጥታ አካላት ተሳትፈዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review