AMN መስከረም 5 /2017 ዓ.ም
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጰያዊነትንን በአንድነት ያሰባሰበ እና ጐልተው እንዲታዩ ያደረገ ኘሮጀክት መሆኑን የኤ ኤም ኤን ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ ገልፀዋል፡፡
ታላቅ የህዳሴ ግድብ ኘሮጀክት በመላው ኢትዮጵያ ያሉ ህዝቦችን በአንድ ያሰባሰበ ነው ያሉት ስራ አስፈፃሚው፣ መሰል ትላልቅ ኘሮጀክቶች ሊደጋገሙ እንደሚገባ ለዚህም ሚዲያዎችም የድርሻቸው ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ተከትሎ የኤ ኤም ኤን አመራሮችና ሠራተኞች በተገኙበት የእንኳን ደስ ያላችሁ መርሀ ግብር ተካሂዷል፡፡
በመርሀ ግብሩ ላይ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የኤ ኤም ኤን ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያዊያንን ያሰባሰበን ፣አንድ ያደረገንና ያጎላ ኘሮጀክት መሆኑን አመላክተዋል።
ኤ ኤም ኤን ይህንን ታላቅ ሀገራዊ አሻራ ያረፈበትን ኘሮጀክት መረጃዎችን ለህዝብ ከማድረስ ጎን ለጎን የተቋሙ ሰራተኞች እና አመራሮች የተሰማቸውን ደስታ የገለፁበት መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።

ኘሮጀክቱ በመጠናቀቁ ደስታቸውን ከመግለጽ በተጨማሪ በሀገራችን ብሎም በከተማችን ለሚከናወኑ ትላልቅ ኘሮጀክቶች ኤ ኤ ም ኤን ለህብረተሰቡ ወቅታዊ መረጃን ተደራሽ በማድረግ ያለመ መድረክ መሆኑን ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል።
ይህንን ከግብ ለማድረስ ያልፈጣሩ እና የተዛቡ መረጃዎችን በማረም እና በማስተካከል ህዝቡ ለልማት እና ለእድገት እንዲነሳሳ የማድረግ ስራውን በማጠናከር ረገድ ሚዲያ የራሱን ሚና መጫወት አለበት ብለዋል።
ሚዲያን በአግባቡ የተጠቀሙ አገራት የተሻለ አገርን ፈጥረዋል ያሉት አቶ ካሳሁን፤ ሚዲያን ላልተገባ ነገር የተጠቀሙ ደግሞ አገራቸውን አፍርሰውል በማለት የሚዲያን ሀያልነት አብራርተዋል።
የድህረ እውነት ላይ እንገኛለን ያሉት ስራ አስፈፃሚው፣ ሁሉም ሰው በእጁ የያዘው መረጃ እውነት እንደሚመስለው ጠቅስው፣ ነገር ግን ህብረተሰቡ መረጃን የሚቀበለበትና የሚያጣራበትን መንገዶች ጠንቅቆ ሊያውቅ እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በዚህ ውስጥ የጋዜጠኞች ድርሻ ትልቅ መሆኑን፣ ህብረተሰቡን ከተዛባ መረጃ ለመታደግ ወቅቱን የጠበቀ፣ ግልጽና ትክክለኛ መረጃን ማቅረብ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
በሔለን ተስፋዬ