የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በስኬት መጠናቀቅ ለቀጣይ አገራዊ የልማት ስራዎችን ለመስራት እንደመረማመጃ መሆኑን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበርያ ፅህፈት ቤት ዋና ስራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ገልፀዋል።
ዋና ስራ አስፈፃሚው ይህንን የገለፁት በህብረት ችለናል፤ አሳይተናል በሚል መሪ ሀሳብ በአድዋ መታሰቢያ በተደረገው የፓናል ውይይት ላይ ነው።
ህዳሴ ግድብን በማሳካታችን ደስ ቢለንም በዚህ ስኬት እንዳንዘናጋ እና ይህንን ድል ለቀጣይ የልማት ጉዟችን መረማመጃ ማድረግ እንዳለብን አጥብቀን ልንመክር፤ ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉ ዋና ስራ አስፈፃሚው አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

መጀመር አንድ ነገር መሆኑን፤ ፈተናዎችን አልፎ መጨረስ ደግሞ ሌላ ነገር መሆኑን ያስረዱት አረጋዊ (ዶ/ር)፤ ከእንግዲህ መቆም የለም ብለዋል፡፡ በራስ አቅም የማደግ ጉዞ ህዳሴ ግድብን በማጠናቀቅ መጀመሩንም አስረድተዋል ።
ብዝሀነት በሰከነ አዕምሮ እና በበሰለ ትልም ሲገራ ጠቃሚ እና ገንቢ መሆኑን የህዳሴ ግድብ አመርቂ ፍፃሜ አስረግጦ አሳይቶናል ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ የግድቡ ለስኬት መብቃት የህዝብ እና መንግስት በመናበብ በመተጋገዝ ለጋራ አላማ አንድ ሆኖ መጓዝ ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ተናግረዋል።
በህብረት ስንነሳ ቀደም ሲል በአድዋ ባሳየነው ህብረብሔራዊ አንድነታችን፤ አሁን ደግሞ በህዳሴ ግድብ ደግመነዋል ያሉት ስራ አስፈፃሚው ናቸው። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያውን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያን እህቶቻችን፣ ወንድሞቻችን አለፍ ሲልም በመላው አለም ለሚገኙ ወዳጆቻችን በግልፅ እንዲታይ አስችሏል ሲሉ ተናግረዋል።
በሔለን ተስፋዬ