በዲሞክራቲክ ኮንጎ በተከሰተ ኢቦላ ወረርሽኝ የ28 ሰዎች ህይወት አለፈ

You are currently viewing በዲሞክራቲክ ኮንጎ በተከሰተ ኢቦላ ወረርሽኝ የ28 ሰዎች ህይወት አለፈ

AMN – መስከረም 6/2018 ዓ.ም

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተከሰተ ኢቦላ ወረርሽኝ የ28 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡

የአለም ጤና ድርጅት በዴሞክራቲክ ኮንጎ የተከሰተውን የኢቦላ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ነው።

በሀገሪቱ “ካሲ” በተባለ አውራጃ በተከሰተው አዲስ ወረርሸኝ እስካሁን የ28 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 16ቱ ሞት የተከሰተው በዚህ ወር መሆኑን አርቲ አስነብቧል።

የአለም ጤና ድርጅት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር እያደረገ በሚገኘው ጥረት “ኢርቭቦ” የተባለ ክትባት ወደ ኪንሻሳ መላኩን አስታውቋል።

በመጀመሪያው ዙር የክትባት ስርጨት 400 ዶዝ ክትባት ወረርሽኙ ወደ ተስፋፋባቸው አውራጃዎች እንደሚላክ ተሰምቷል።

አለም አቀፍ ድጋፍ ሰጪ አካላትን በማስተባበር 45 ሺህ ዶዝ ተጨማሪ ክትባት በቅርቡ ወደ ስፍራው እንደሚልክ ያስታወቀው ድርጅቱ፤ 48 የጤና ባለሙያዎችን ማሰማራቱንም አመላክቷል።

እንደ ኮንጎ የጤና ሚኒስቴር መረጃ ከሆነ ከ1976 ጀምሮ በሀገሪቱ 16 ጊዜ የኢቦላ ወረርሽኝ ተከሰቷል።

ከዚህ ባለፈም የወረርሽኙን ድንበር ተሻጋሪነት እና ስርጭት ለመቀነስ በጎረቤት ሀገራት ድንበር ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር እና ዝግጅት እንዲደረግ የአለም ጤና ድርጅት አሳስቧል።

በቅርቡ በተመሳሳይ በዩጋንዳ በተከሰተ ወረርሽኝ 14 ተጠቂዎች እና 4 ሞት መመዝገቡ ይታወሳል።

ባለፉት አስርት አመታት በጦርነት እየታመሰች በምትገኘው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተደጋጋሚ የሚከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ ተጨማሪ ራስ ምታት ሆኗል።

ከፍተኛ የመተላለፍ አቅም ያለው የኢቦላ ወረርሽኝ፤ ራስ ምታት ፣ ማስመለስ ፣ የሰውነት ማሳከክ እና መቁሰል ፣ እንዲሁም በተለያየ አካላት የደም መፍሰስ ምልክቶቹ እንደሆኑ የአለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review