የትጋት ተምሳሌቷ ተማሪ

You are currently viewing የትጋት ተምሳሌቷ ተማሪ

AMN – መስከረም 6/2018 ዓ.ም

‎ይህ ውጤት ባስተማሯት ተማሪ መመዝገቡ ኩራት እንደተሰማቸው ይናገራሉ። የመምህር እርካታው ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸው መሆኑን ያስረዳሉ።

‎ለውጤት መብቃቷ አንገቷን ደፍታ በማጥናቷ መሆኑን ይመሰክሩላታል፤ ትምህርት ህይወቷ ነውም ይላሉ መምህሯ። ለውጤት የመብቃቷ ሚስጥር ከጥናት በተጨማሪ ስነምግባር የተላበሰች ተማሪ መሆኗ ነው ይላሉ የብስራተ ገብርኤል ትምህርት ቤት የፊዚክስ መምህር አንዷለም አየለ።

‎ተማሪ ሀይማኖት ዮናስ አገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተና ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ሁለተኛ ናት። ተማሪ ሃይማኖት በመልካም ሥነ-ምግባር የታነፀች ጭምር እንደሆነች መምህሯ ገልፀው፤ ይህ ውጤት ለእርሷ አዲስ እንዳልሆነ እና እንደሚገባት ተናግረዋል።

‎በክፍሏ ውስጥ መምህር ሲያስተምር በትክክል የምታዳምጥ እና ለምትጠየቀው ጥያቄ ተገቢውን መልስ ለመስጠት የምትታትር ተማሪ መሆኗን ይገልፃሉ። ሃይማኖት ሁልጊዜ የምታጠና፣ በራሷ የምትተማመን፣ ያላትን ዕውቀት ለሌሎች ለማጋራት ወደ ኋላ የማትል ብቁ ተማሪ መሆኗን ገልፀዋል።

‎ተማሪ ሃይማኖት ዮናስ በበኩሏ፤ ለዚህ ውጤት የበቃሁት ትምህርቴ ላይ ትኩረት ከማድረግ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም የወጡ ፈተናዎች አወጣጥን በተደጋጋሚ በማየት ላይ አተኩራለሁ ብላለች። በትምህርት ሰዓት መምህራን የሚያስተምሩትን ከመከታተል በተጨማሪ፣ በቤት ማጥናት የዕለት ተዕለት ስራዋ መሆኑን ገልፃለች።

‎ሰዓቷን በአግባቡ በመጠቀም የመትታወቀው ሀይማኖት፣ ለዚህ ስኬት እንድትበቃ ከራሷ ጥረት በተጨማሪ የቤተሰቦቿ፣ የመምህራን እና የትምህርት ቤቱ እገዛ እንዳልተለያት ተናግራለች። ተማሪ ሃይማኖት እንደተናገረችው ፣ ይህንን ውጤት ለማምጣት ከስር መሰረቷ ጀምሮ እጅግ ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበች፤ ከአጠቃላይ ክፍሎች 1ኛ በመውጣት እየተሸለመች 12ኛ ክፍል መድረሷን ተናግራለች።

‎ለቀጣይ የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ያዋጣኛል የሚሉት የጥናት ዘዴ ላይ በማተኮር ለውጤት መብቃት እንደሚችሉ ገልፃ፤ ከወዲሁ ሰዓታቸውን በአግባቡ በመጠቀም ከፍተኛ ውጤት ማምጣት ይችላሉ በማለት መልዕክቷን አስተላልፋለች።ለወደፊቱ ኒሮሳይንቲስት በመሆን ያስተማረኝን ቤተሰቤን ብሎም አገሬን የማገልገል ትልም አለኝ ብላለች።

‎የብሥራተ ገብርኤል ትምህርት ቤቶች ካስፈተናቸው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል አንዷ የሆነችው ተማሪ ሃይማኖት፣ በተፈጥሮ ሳይንስ 579/600 በማግኘት በሀገር አቀፍ ደረጃ 2ኛውን ከፍተኛ ውጤት አምጥታለች።

‎በሔለን ተስፋዬ

#Ethiopia

#addisababa

#education

#AMN

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review