በቅርቡ 21 የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች ወደ ሥራ እንደሚገቡ የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አስታወቀ።
በፌዴራል ደረጃ በመሶብ የአንድ ማዕከል የሚሰጡ አገልግሎቶች 180 መድረሳቸውም ተገልጿል። የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ሃይሌ(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የመንግስት አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ሪፎርም አንድ አካል የሆነው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተገልጋዮችን ቅሬታና እንግልት በመቀነስ ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው።
የመንግስት አስተዳደርንና አገልግሎት አሰጣጥ በማሻሻል ዘመናዊ ሲቪል ሰርቪስ ለመገንባት መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት። በአንድ ማዕከል የሚሰጡ አገልግሎቶች ሙሉ ለሙሉ በዲጂታል መንገድ ሲሆን፤ ለአገልግሎት አሰጣጡ የራሱ ልኬት ተቀምጦለታል ብለዋል።
አንድ ብሎ የጀመረው የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እየተስፋፋ መምጣቱን አመልክተው፤ ይህም እስከ መስከረም 2018 ዓ.ም መጨረሻ ማዕከላቱን 21 በማድረስ ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል ብለዋል። በኢትዮጵያውያን የበለጸገውና አገልግሎቶቹን የሚያስተሳስረው ቴክኖሎጂ አስተማማኝ መሆኑን ጠቁመው፤ በርካታ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉንም ነው ኮሚሽነሩ የተናገሩት።
በመላ ሀገሪቱ ቢያንስ አንድ የመሶብ አገልግሎት እንዲኖር እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ማዕከላቱን በክልሎች የማስፋፋት እቅድ መኖሩንም ገልጸዋል። በፌዴራል ደረጃ 180 የደረሰው የአገልግሎቶች አቅርቦት በክልሎች ከፍተኛው 50 ዝቅተኛው ደግሞ 10 መሆኑንም አነስተዋል።
እንደኮሚሽነሩ ገለጻ፣ በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በርካታ ተገልጋዮች ደስተኛ መሆናቸውንና ይህም የመልካም አስተዳደርና የብልሹ አሰራር ችግሮችን በመፍታት በኩል ሁነኛ መፍትሔ ሆኗል ማለታቸዉን ተዘግቧል፡፡ የማዕከሉን አገልግሎቶች በማስፋት የተገልጋዩን እርካታ የበለጠ ለማሳደግ እንደሚሰራም ነው ኮሚሽነሩ ጨምረው ያረጋገጡት።