የመደመር መንግስት መጽሃፍ የኢትዮጵያ ችግሮችን በጥልቅ የዳሰሰና መፍትሄ ያመላከተ መሆኑን አቶ ጌታቸው ረዳ ገለፁ

You are currently viewing የመደመር መንግስት መጽሃፍ የኢትዮጵያ ችግሮችን በጥልቅ የዳሰሰና መፍትሄ ያመላከተ መሆኑን አቶ ጌታቸው ረዳ ገለፁ

AMN – መስከረም 7/2018 ዓ.ም

የመደመር መንግስት መጽሃፍ የኢትዮጵያ ችግሮችን በጥልቅ የዳሰሰና መፍትሄ ያመላከተ ነው ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ ገለጹ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተጻፈው የመደመር መንግስት መጽሃፍ ለንባብ በቅቷል።

በመጽሐፍ የምረቃ መርሐ-ግብር ላይ ፕሬዝዳነት ታዬ አጽቀስላሴ፣ የመጽሃፉ ደራሲና የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች፣ እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል።

በመጽሐፍ ላይ ዳሰሳ ካቀረቡት መካከል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ እንዳሉት፣ መጽሃፉ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ሁኔታ የሚያስቃኝ ነው። በተለይ የኢትዮጵያ ችግሮችን በጥልቅ የዳሰሰ እና ተግባራዊ መፍትሄዎችን ያመላከተ መሆኑንም ተናግረዋል። መጽሃፍ አስተሳሰብ ላይ ትኩረት አድርጎ ከቁጭት እንደሚነሳ ጠቅሰው፣ ይህም ችግሮችን ከመሰረቱ ለመፍታት ወሳኝ መሆኑን ነው ያብራሩት።

መጽሃፉ ነገሮችን አፍርሶ ከመስራት ይልቅ አዎንታዊውን ማስቀጠል፣ አሉታዊውን ደግሞ ማስተካከልን እንደሚያመላክትም ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል። ይህም ኢትዮጵያ ለዘመናት የሄደችበትን ተቸካይ የፖለቲካ አካሄድ የቀየረ አተያይ ስለመሆኑም አብራርተዋል። መጽሃፉ ፖለቲካችን ያሸነፈ አካል እንደፈለገ ሁሉን ይጠቅልል ከሚል አካሄድ የሚያወጣ ነው ብለዋል።

”እኔ የፈለኩት ካልሆነ” ከሚል የዜሮ ድምር ጨዋታ መውጣት የሚቻልበትን ዘመናዊ የፖለቲካ አካሄድ ያመላከተ ስለመሆኑም አቶ ጌታቸው አብራርተዋል። በሌላ በኩል ዜጎች ከመሰረታዊ ፍላጎት ባሻገር በክብር የመኖር ህልማቸውን ለመመለስ አቅጣጫ ያስቀመጠ መሆኑንም እንዲሁ። የኢትዮጵያ ችግሮች በነበረው አካሄድ ትርጉም ባለው መልኩ መፍታት እንደማይቻል አንስተው፣ የመደመር እሳቤ ተግባራዊ ያደረገው መፍጠርና መፍጠን በዚህ ረገድ ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማን የተከማቸ ችግር ለመፍታት የተተገበረው የመፍጠርና መፍጠን መፍትሄ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ መሆኑንም ተናግረዋል። አዲስ አበባን ለመለወጥ የተጀመረው ስራ አዲስ የስራ ባህልን ያለማመደ መሆኑንም ገልጸዋል።በቀጣይ በአዲስ አበባ የታየው አዲስ ተስፋ ወደ ሁሉም የኢትዮጵያ አቅጣጫ እንዲሰፋ መረባረብ ይገባል ነው ያሉት። መጽሃፉ ለማንበብ ምቹ በሆነ አቀራረብ መዘጋጀቱን የተናገሩት አቶ ጌታቸው፣ ሁሉም እንዲያነበውም ጥሪ አቅርበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review