የመደመር መንግሥት ከትናንት እስረኝነት የተላቀቀና ለምክንያታዊነት ትኩረት የሰጠ መሆኑን በመደመር መንግሥት መጽሃፍ ላይ ሂሳዊ ዳሰሳ ያቀረቡ ምሁራን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በመደመር እሳቤ የጻፉት 4ኛው መጽሃፍ ”የመደመር መንግሥት” ተመርቆ ለንባብ በቅቷል።
በመጽሐፍ የምረቃ መርሐ-ግብር ላይ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ፣ የመጽሃፉ ደራሲና የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች፣ እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል።
በመጽሃፉ ላይ ዳሰሳ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ዳኛቸው አሰፋ(ዶ/ር)፣ መጽሃፉ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ችግሮች ላይ ንደፈ ሃሳባዊ ትንተና ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ ምላሽ የሚያመላክት መሆኑንም አብራርተዋል።

ለችግሮች አውዱን የተገነዘበ ሙሉ መፍትሄ ማስቀመጥ እንደሚገባ በመጽሃፉ በግልጽ መቀመጡን ጠቅሰው፤ ይህም አንድ መንገድን ብቻ ከሚከተል የርዕዮት እስረኝነት የተላቀቀ አካሄድ ነው ብለዋል። መጽሃፉ የያዛቸው ትንተናዎች በምክንያታዊነት ላይ ያረፉና ለምክንያታዊነት ክፍት መሆናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።
መጽሃፉ ኢትዮጵያ አሁን ላይ የት እንዳለችና መጻኢ ጉዞዋ ምን መምሰል እንዳለበትም በግልጽ ያስቀምጣል ነው ያሉት። በተጨማሪም በዜጎች መካከል መተባበርና መደጋገፍ እንዲኖር መንገድ በማሳየት ሰላምና አብሮነት እንዲጎለብት ዝርዝር ሃሳብ ማስቅመጡንም አንስተዋል።

ሌላኛው በመጽሃፉ ላይ ሂሳዊ ዳሰሳ ያቀረቡት የፖለቲካ ተንታኙ ዘሪሁን ተሾመ በበኩላቸው፤ መጽሃፉ ትናትን በልኩ የሚገነዘብና በትናንት እሳቤ ላይ ያልቆመ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
የዛሬ ችግሮችን በተገቢው መንገድ እንደሚዳስስ ጠቅሰው፤ የሚያጋጥሙ ፈተናዎች የተሻለ ነገን ከመገንባት የሚያስቆሙ እንዳልሆኑ በግልጽ እንደሚያመላክትም ነው ያነሱት።
በመጽሃፉ የተዳሰሱ ሃሳቦችም ከኢትዮጵያ ባለፈ ለአፍሪካ የሚበጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።