ዶዶላን የውጤት እና የስኬት መፍለቂያ ያደረገው ምሰጢር ምን ይሆን?

You are currently viewing ዶዶላን የውጤት እና የስኬት መፍለቂያ ያደረገው ምሰጢር ምን ይሆን?

‎AMN- መስከረም 08/2018 ዓ.ም

‎ኦሮሚያ የአትሌቶች ብቻ ሳትሆን የምሁራን መፍለቂያም ነች።

‎በተለይ በእውቀትና በስነ ምግባር የታነጸ ሃገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍረት ለትምህርት ዘርፍ በተሰጠው ትኩረት አበረታች ለውጥ በመመዝገብ ላይ ይገኛል። በተለይ በኢፋ ቦሩ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች : በኦሮሚያ ልማት ማህበር እና በሌሎች ትምህርት ቤቶች እየተመዘገበ ያለው ውጤት ለዚህ ማሳያ ነው።

‎በዶዶላ ኢፋ ቦሩ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ዘንድሮ የተመዘገበው ውጤት ደግሞ በአይነቱ ልዩ እንደሆነ የብዙሃኑ መነጋገሪያ ሆኗል። በ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሃገር አቀፍ ፈተና በሁለቱም ጾታ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡት ተማሪዎች ከዚሁ ትምህርት ቤት የተገኙ ናቸው። ከትምህርት ቤቱ 50 እና ከዚያ በላይ የማለፊያ ውጤት ያስመዘገቡት 72 ተማሪዎች ሲሆኑ ለፈተና የተቀመጡ ተማሪዎችን በሙሉ አሳልፏል።

‎ከትምህርት ቤቱ ተማሪ ካሊድ በሽር 591 እንዲሁም ተማሪ ገነት መርጋ 579 ነጥብ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ሲሆን 580 እና 570 አጠቃላይ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችም በርካቶች ናቸው። ለመሆኑ የትምህርት ቤቱ የስኬት ምስጢር ምን ይሆን? ዶዶላ ኢፋ ቦሩ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ከሶስት አመታት በፊት ተመርቆ የመማር ማስተማር ስራውን የጀመረው ከአርሲ: ከምዕራብ አርሲ : ከባሌ: ከምስራቅ ባሌና ምስራቅ ሸዋ የመጡ ተማሪዎችን በመቀበል ነበር።

‎ትምህርት ቤቱ ባለፉት ሶስት አመታት በእውቀትና ሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ ውጤቱን ማጣጣም ጀምሯል። ‎የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር መምህር ዴቱ ዲቦ ዋንኛው የስኬቱ ምስጢር በቁርጠኝነት መስራት ነው ሲሉ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ተናግረዋል።

‎የ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሃገር አቀፍ ፈተና የወሰዱት 125 ተማሪዎች በሙሉ ሲያልፉ ከነዚህ መካከል 500 እና ከዚያ በላይ ያመጡት ተማሪዎች ደግሞ 72 መሆናቸውን ገልጸዋል። የትምህርት ቤቱ መምህራንና ተማሪዎች በትጋትና ቁርጠኝነት በመስራት ይህንን ውጤት ማስመዝገባቸውን ያብራሩት ርዕሰ መምህሩ በተለይ መምህራን ተማሪዎችን ከማብቃት ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

‎ተማሪዎቹ በሥነ ምግባር የታነጹ መሆናቸው ደግሞ የመምህራኑ ትጋትና ድካም ፍሬ እንዲያፈራ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። ተማሪዎቹ ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም እና አስቀድመው ለፈተና በመዘጋጀት ከፍተኛ ውጤት ሊያስመዘግቡ እንደቻሉም ጨምረው ገልጸዋል።

‎የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር መምህር ዴቱ ዲቦ እንደተናገሩት ከሆነ በ2018 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሃገር አቀፍ ፈተና የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ከአምናው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ መምህራንና ተማሪዎችን ጨምሮ ወላጆችና የትምህርት ባለድርሻ አካላት በሙሉ ከወዲሁ በቁርጠኝነት እየተሠሩ ነው።

‎በመልካሙ አበበ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review