የመቃብር ቆፋሪዎች ውድድር የምታካሂደው አውሮፓዊት ሀገር

You are currently viewing የመቃብር ቆፋሪዎች ውድድር የምታካሂደው አውሮፓዊት ሀገር

AMN – መስከረም 9/2018 ዓ.ም

በአለም ላይ በርካታ አስደናቂ እና አስገራሚ ውድድሮች ሲካሄዱ ተሰምቷል። የመቃብር ቆፋሪዎች ፍጥነት እና የማስዋብ አቅምን የሚፈትን ውድድር መካሄድ ግን ለብዙዎች እንግዳ እና አስገራሚ ዜና ነው።

8ኛው አለም አቀፍ የመቃብር ቆፋሪዎች ውድድር በሀንጋሪ ተካሂዷል። ከ2016 ጀምሮ መከናወን የጀመረው ውድድሩ፤ በአለም አፍ ደረጃ በቀብር መቆፈር ስራ ላይ ወይም በጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ መቃብር ቆፋሪዎች ይሳተፉበታል ።

የሀንጋሪ የመቃብር ቆፋሪዎች እና ተንከባካቢዎች ማህበር ውድድሩን ማከናወን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በኮሮና ምክንያት ከተሰረዘበት ሁለት አመታት በስተቀር ውድድሩን በቋሚነት እያከናወነ ይገኛል። በውድድሩ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ጥንድ ጥንድ ቆፋሪዎች ፍጥነት ፣ ውበት እና አጨራረስ መስፈርት በወጣለት ውድድር ለአሸናፊነት ይፎካከራሉ ። ተወዳዳሪዎች 2 ሜትር ርዝመት ፣ 80 ሴ.ሜ ስፋት እና 1.6 ሜትር ጥልቀት ያለው መቃብር ከሁለት ሰዓት ባነሰ ጊዜ ቆፍረው መጨረስ ይጠበቅባቸዋል ።

ቀጥለውም 2.5 ቶን የሚመዝነውን ከጉድጓድ የወጣ አፈር ወበቱን በጠበቀ መልኩ ወደ ጉድጓድ በተገቢው መንገድ መመለሳቸው ለፈተና ይቀርባል ። በዘንድሮው አመት ውድድር የሀንጋሪው ፓራክሊቶዝ ለትርፍ ያልተቋቋመ የመቃብር ቁፋሮ አገልግሎት ለተከታታይ ሁለተኛ አመት አንድ ሰአት ከ30 ደቂቃ በፈጀ ጊዜ በማጠናቀቅ የአንደኝነቱን ስፍራ ይዟል።

አሸናፊዎቹ በበጎ ፈቃድ የመቃብር ቁፋሮ ስራ ላይ መሰማራታቸው እና ስራውን በየቀኑ የሚሰሩት ስራ መሆኑ ለአሸናፊነታቸው ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል። በዘንድሮው ውድድር ላይ ሩስያን ወክለው የተሳተፉ ቆፋሪዎች በውድድሩ የመጨረሻ ደረጃን ሲይዙ የሀገሪቱን ሞቃት አየር ለውጤት ማጣታቸው ምክንያት አድርገውታል።

የአለም አቀፍ የመቃብር ቁፋሮ ሻምፒዮና ውድድር ዓላማ የሙያውን ክብር ከፍ ማድረግ፣ ወጣቶችን ወደ ሥራው መሳብ እና ችሎታቸውን ማሳየት ነው ተብሏል። በተጨማሪም አዘጋጆቹ የአካል ብቃት ብቻ ሳይሆን የአዕምሮ ጥንካሬን የሚጠይቀውን የመቃብር ቆፋሪዎችን ታታሪነት ለማስገንዘብ አላማ አድርገው እንደሚያዘጋጁት ገልጸዋል።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review