በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ያሳያነውን ትብብርና ድጋፍ በማጠናከር በሌሎች ልማቶችም መድገም አለብን ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ተናገሩ።
የሕዳሴው ግድብ ግንባታ መጠናቀቅን አስመልከቶ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቦንጋ ከተማ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ዛሬ ተካሂዷል።
ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያውያን የዘመናት ቁጭት የሆነው የአባይን ውሃ የመጠቀም ጥያቄ በሕዳሴው ግድብ ምላሽ አግኝቷል ብለዋል።
በጠንካራ መሪዎችና በሕዝቡ ትብብር እውን የሆነው የሕዳሴ ግድብ በአንድ ያስተሳሰረን የወል ቅርስ ነው ሲሉም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በግድቡ ግንባታ ያሳየነውን ትብብርና ድጋፍ በማጠናከርና ያሉንን ሀብቶች በተገቢው በመጠቀም በሌሎች ልማቶች ላይ መድገም አለብን ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የክልሉ ሕዝቦች በግድቡ ግንባታ ወቅት በተለያየ መልኩ ላበረከቱት አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል።
የካፋ ዞን አስተዳደሪ እንዳሻው ከበደ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያውያን አይበገሬነት ዛሬም ቀጥሎ ሕዳሴን የመሰለ ታላቅ ፕሮጀክት እውን ማድረግ ችለናል ብለዋል።
በቀጣይም የዞኑ ሕዝብ በሕዳሴው ግድብ ያሳየውን ሕብረትና አንድነት በሌሎች የልማት ተግባራት ላይም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።