የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ልዑክ ቡድን ከአቡዳቢ የሰላም ፎረም ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጉን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕሮፌሰር) በዚሁ ጊዜ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የተቋቋመበትን ዓላማ እንዲሁም እስካሁን ያደረገውን ጉዞ ለፎረሙ አባላት አስረድተዋል፡፡ ዋና ኮሚሽነሩ ኢትዮጵያ ልዩነቶቿን በምክክር በመፍታት ሙሉ ትኩረቷን ወደ ልማት ለማዞር በመጨረሻው ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡
የአቡዳቢ የሰላም ፎረም ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ከሊፋ አልዳህሪ በበኩላቸው ፎረሙ በሰላም ዙሪያ ስለሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራት ለልዑክ ቡድኑ ገለጻ አድርገዋል፡፡ በተለይ ነባር የሰላም እሴቶችን በማጠናከር እና አሰባሳቢ ትርክት በማምጣት በቀጠናው የጽንፈኝነትን አስተሳሰብ ማዳከም ስለተቻለበት መንገድ የፎረሙን ተሞክሮ አጋርተዋል፡፡
ዋና ጸሐፊው የኢትዮጵያ የምክክር ሂደት የተሳካ እንዲሆን ያላቸውን መልካም ምኞት በመግለጽ ፎረሙ አስፈላጊውን የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ ፎረሙ በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ከሚገኘውና በዓለም አቀፍ የሰላም ግንባታ እና አካታች ውይይት ላይ ትኩረቱን አድርጎ እንደሚሰራ ከኮሚሽኑ የማህበራዊ ድረገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዶ/ር ዑመር ሁሴን በበኩላቸው በሁለቱ ተቋማት መካከል የተደረገው ውይይት በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ጥልቅ የሁለትዮሽ ወዳጅነት አድማሱን ወደ ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እያሰፋ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ ውይይቱ የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ሂደት እስኪጠናቀቅ ሁለቱ ተቋማት ልምድ እንዲለዋወጡና በሌሎች ቴክኒካዊ ትብብሮች ላይ በጋራ እንዲሰሩ ከመግባባት ላይ በመድረስ ተጠናቋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና አካባቢው ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ የሚያሰባስብበት የምክክር መድረክ ነገ ቅዳሜ መስከረም 10/2018 ወይም ሴፕቴምበር 20/2025 ከሰዓት በኃላ 3፡00 PM ጀምሮ Jumeirah Creekside Hotel, Al Garhoud Dubai የሚካሄድ ይሆናል፡፡