AMN- መስከረም 9/2018 ዓ.ም
ከ15 ዓመታት በላይ በቦሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ፍቅርተ አለሙ ልጆቻቸው እንደ ልብ እንደማይጫወቱ ይገልፃሉ። አከባቢው ለማዕድን ማውጫ ተብሎ የተቆፈሩ ጉድጋዶች በክረምት ውሀ ሞልተው ለልጆቻቸው ሰቀቀን መሆናቸውን ይናገራሉ።
በመዲናይቱ ለ10 እና ለ20 ዓመታት ለግንባታ ማዕድን ማውጫ ተቆፍረው በመልሶ ማልማት ያልተደፈኑ ጉድጓዶች ለወ/ሮ ፍቅርተ ብቻ ሳይሆን በአካበቢው ለሚገኙ ሌሎች ነዋሪዎችም ስጋት ሆነው ዛሬም ቀጥለዋል። አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች እንደሚሉት ለማዕድን ማውጫ ተቆፍሮ ለዓመታት ሳይለማ የቆየው መሬት ለአደጋ አጋልጧቸዋል። ህጻናትና እንስሳት በውሃ ሰጥመው ህይወታቸው ከመጥፋቱ በተጨማሪ ለጤና ጠንቅ ሆኖብናል ሲሉ አክለውበታል።
የከተማዋ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ጠላቂ ዋናተኛ አቶ ሙሉጌታ ውዱ እንደተናገሩት፣ በተለያዩ ጊዚያት የሰውን ህይወት ለመታደግ በአካባቢው ብዙ ጊዜ መሰማራታቸውን ተናግረው።

የማዕድን ማውጫ ፍቃድ አሰጣጥ አዋጅ ቁጥር 678/2010 እና አዋጅ ቁጥር 816/2013 የሚሉ ሁለት አዋጆች እንዳሉት የሚገለጹት የህግ ባለሙያው አቶ ዮናስ ሽመልስ፣ በቸልተኝነት ለሚደርሰው ጉዳት በየደረጃው ተጠያቂነት እንደሚያስከትል እና ለመልሶ ማልማት በቂ በጀት ስለመያዙ ቀድሞ መታወቅ እንዳለበት ያብራራሉ፡፡
የህግ ባለሙያው አክለውም፣ በአዋጁ መሰረት የወንጀል ኃላፊነት ከማስከተሉ በተጨማሪ፣ የነፍስ ካሳን የመክፍል አስቻይ የህግ ማቀፍ መኖሩን ይጠቅሳሉ፡፡
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጠን ቁጥጥርና እርምጃ መጠናከር፤ ፍቃድ መሰረዝ፣ የማዕድን ማውጫ መሬቱ ለጤናና ለህይወት ስጋት በማይሆንበት ደረጃ ላይ መሆኑ ሳይረጋገጥ ፍቃድ ማስመለስ እንደማይገባ ተናግረዋል፡፡ የአዲስ አበባ ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት የክዋኔ ኦዲት እንዳረጋገጠው የማዕድን ማውጫ የነበረ 223 ሺህ ካሬ መሬት ተመልሶ ሳይለማ የጉዳቱ ሰለባ ሆኗል።

የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አሰግደው ኃ/ጊዮርጊስ እንደሚሉት፣ የቆየና በጊዜው ያልታረመ አሰራር ክፍተት መኖሩን አስታውሰው፣ በፍጥነት ለማስተካከል እየተሰራበት ነው ብለዋል።
55 ችግር ያለባቸው ቦታዎች ተለይተው 19 አልሚዎችን በማስጠንቀቅ ወደ ልማት ገብተዋል ያሉት ምክትል ስራ አስኪያጁ፣ 36ቱ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ የቅጣት እርምጃ ተወስዶባቸዋል ብለዋል።
አቶ አሰግደው አክለውም፣ ዘላቂ መፍትሔው ከከተማ አስተዳደሩ ፕላን ኮሚሽን ጋር በመነጋገርና በደብዳቤ በማሳወቅ በከተማዋ ማስተማር ፕላን መሰረት ሁሉም ለማዕድን ማውጫ ተብለው የተቆፈሩ ቦታዎች ወደ ልማት ገብተው የህዝብ ስጋትና አደጋ ከመሆን ተላቀው ወደ መዝናኛነት ይቀየራሉ ብለዋል፡፡
በአለኸኝ አዘነ