ወንጀሉ የተፈፀመው ነሐሴ 27 ቀን 2017 ዓ/ም በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ልዩ ቦታው ኮተቤ እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ ነው።
ዶክተር አበባው በላይነህ የተባለው ይህ ግለሰብ ከሚሰራበት ኮተቤ ጤና ጣቢያ አካባቢ ባልታወቁ ሰዎች ታግቶ የተወሠደ በማስመሰልና በገዛ ስልኩ አጋቾች እንደጻፉ በማስመሠል ለትዳር አጋሩ “ሦስት ሚሊዮን ብር እንዲያመጡ ይህን ካላደረጉ በህይወት እንደማይገኝ የሚገልጽ የጽሁፍ መልዕክት ይልካል፤ ቤተሠብም በወቅቱ በመደናገጥ ጉዳዩን ለፖሊስ አመልክተዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የተደራጁና የልዩ ልዩ ወንጀሎች ምርመራ መምሪያ የደረሰውን አቤቱታ መነሻ በማድረግ ጥቆማው ከደረሰው ሠአት ጀምሮ የምርመራ ክፍሉና የክትትልና ኦፕሬሽን ቡድኑ በመቀናጀት ተገቢውን የክትትል ስራ በመስራት ታግቻለው ያለው ግለሰብ ደብረ ብርሀን ከተማ ከአንድ ሆቴል ውስጥ እንዳለ ይደርሱበታል።
በሆቴሉ ደርሰው ሲያጣሩም ግለሰቡ ለሦስት ቀናት ቆይቶ መሄዱን መረጃ ያገኛሉ። ፖሊስ ለምርመራው እንዲረዳም የባንክ እንቅስቃሴውን እየተከታተለ መሆኑን የተረዳው ተጠርጣሪ ጳግሜ 1 ቀን 2017 ዓ/ም ከቀኑ 10 ሠአት ገደማ አጋቾቹ ብሩ ሊላክላቸው ባለመቻሉ ለቀውኛል በሚል ከሦስት ቀናት ቆይታ በኋላ ወደ መኖሪያ ቤቱም ተመልሷል። ፖሊስም ግለሰቡ ወደ ቤተሠቡ መመለሱን በደረሠው መረጃ በቁጥጥር ስር ሊያውለው መቻሉን የምርመራ መዝገቡ ያስረዳል።
ፖሊስም ግለሰቡ ላይ ባደረገው ምርመራ የማስፋትና ስራ ታገትኩ ያለው ግለሰብ ምንም ዓይነት የእገታ ወንጀል ያልተፈፀመበት መሆኑን እና ገንዘቡን የጠየቀውም እራሱ መሆኑን፣ ለሦስት ቀናት ሆቴል አልጋ ይዞ እንደቆየም ጭምር በተደረገው ምርመራ ሊደረስበትም ችሏል።
አንዳንድ ግለሰቦች ያልተገባን ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ያልተፈጸመባቸውን ወንጀል ተፈጽሞብኛል በማለት በሌሎች ሰዎች ላይ ፍርሀትን ከመንዛትም ባለፈ የሚፈፅሙት ድርጊት ከህግ ተጠያቂነት እንደማያድናቸው ሊገነዘቡ ይገባል ሲል የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለኤኤምኤም በላከዉ መረጃ መልዕክቱን ያስተላልፏል፡፡