በመነቃቃት ላይ ያለው የምሽት ንግድ

You are currently viewing በመነቃቃት ላይ ያለው የምሽት ንግድ

ንግዱ የከተሜነት አንዱ መገለጫ መሆኑ ተጠቁሟል

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በአዲስ አበባ እየተሻሻለ የመጣው በጊዜ እና በሁኔታ ያልተገደበ ንቁ የሥራ እንቅስቃሴ ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡ አምረውና ምቹ ተደርገው የተገነቡ የመንገድ መሰረተ ልማቶች፣ ከመሬት የፈሰሰን ጤፍ ማስለቀም የሚችሉት የመንገድ ዳር መብራቶች፣ አስተማማኝ የሆነው ፀጥታና ደህንነት … ሌሊቱን የቀን ገፅታ አላብሰውት የምሽት የሥራ እንቅስቃሴ በስፋት እና በንቃት እንዲከወን አግዘዋል፡፡ ይህንን ዕውነታ ለመገንዘብ፤ አመሻሽ ላይ ከቤት ወጣ ብሎ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች መንቀሳቀስ ይበቃል፡፡ ቦሌ ቢሉ መገናኛ፣ አራት ኪሎ ወይም ፒያሳ፣ ሽሮሜዳ እና መርካቶ… አመሻሽ ላይ ከተገኙ፤ የንግድ እና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በቀን በነበረው የሥራ እንቅስቃሴ ውስጥ ይመለከቷቸዋል፡፡

እኛም በምሽት ተዘዋውረን ያረጋገጥነው እውነት፤ አዲስ አበባ እና አዲስ አበቤ በጊዜ ያልተወሰነ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባታቸውን ነው። የሀገር ባህልን በጥበብ ሸምነው እና አስጊጠው በአልባሳት፣ በጌጣጌጥ፣ በቁሳቁስ ወዘተ መልክ ወደሚያቀርቡት ጠቢባን ሠራተኞች መገኛ ሽሮሜዳ፤ ምሽት 2፡30 አካባቢ ተገኝተን የተመለከትነው፤ ምሽትም ሁነኛ የሥራ ጊዜ እየሆነ መምጣቱን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በሥፍራው በተገኘንበት ሰዓት፤ በአካባቢው ያሉት ሱቆች ክፍት ነበሩ። ነጋዴዎቹ ደንበኞቻቸውን ተቀብሎ ለማስተናገድ ድካም በማይታይበት ንቃት ይጠባበቃሉ፤ የመጡትንም ያስተናግዳሉ።

አቶ ደረጀ ገመቹ በሽሮ ሜዳ የሀገር ባሕል ልብስ መሸጫ ሱቅ አላቸው። በዚህ ሥራ ከተሠማሩ ከአስር ዓመት በላይ አስቆጥረዋል፡፡ እኛም አመሻሽ ላይ ወደዚያ ባቀናንበት ወቅት  በሥራቸው ላይ አግኝተን አነጋግረናቸዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፤ የሽሮሜዳ የሥራ እንቅስቃሴ በወቅትና በሁኔታ የተገደበ ነው፡፡ የሀገር ባህል አልባሳት፣ ጌጣ ጌጦች፣ ሌሎች መሰል ቁሳቁሶች የሚቀርቡበት የገበያ ሥፍራ በመሆኑ፤ የተለያዩ በዓላት (ጥምቀት፣ መስቀል፣ ፋሲካ…)፣ በሀገር አቀፍ እና በከተማ የሚከበሩ እንደ ብሔር ብሔረሰቦች ያሉ በዓላት እንዲሁም በተለመዱ የሠርግ ወቅቶች ገበያው በአንፃራዊነት ጥሩ የሚባል ነው። በሌሎቹ ጊዜያት ያለው የግብይት ሁኔታ ቀዝቀዝ ያለ ቢሆንም፤ ሥራ የለም በሚል ለምሬት የሚያበቃ አይደለም፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ የሀገር ባሕል ልብስ የመጠቀም ልምድ እና ፍላጎት እያደገ መምጣቱን የሚጠቁሙት አቶ ደረጀ፤ በሽሮ ሜዳ ያለው ነጋዴ በሚያደርገው የሥራ ፉክክር፣ የደንበኞች ፍላጎት ማደግ፣ ዘመናዊ ዲዛይኖች በፍጥነት እና በብዛት መምጣታቸው የገበያው እንቅስቃሴ መሻሻል እንዲያመጣ ማድረጉን ያነሳሉ። በቅርቡ ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው የኮሪደር ልማት የሽሮ ሜዳን የገበያ ሥፍራ የበለጠ ውበት እና ምቾት እንዳጎናፀፈው ይመሰክራሉ፡፡ ከልማቱ ጋር በሚስማማ መልኩ ሱቆች እንዲታደሱ መደረጉ እንኳን ለደንበኞች ለነጋዴውም የሚያስደስት የሥራ አካባቢን ፈጥሯል፡፡ የመንገድ ዳር መብራቶች በአዲስ መልኩ መግባታቸው፣ በየሱቆቹ የውጪ መብራት መገጠማቸው በቅርቡ የጀመርነውን የምሽት ሥራ ስኬታማ አድርጎታል፡፡ ማንኛውም ሰው ከደህንነት ስጋት ውጪ ሆኖ የሚንቀሳቀስበት አካባቢ ሆኗል፡፡ ይህም በቀጣይ፤ ህብረተሰቡ እየለመደው ሲመጣ የምሽት ገበያ ውጤታማነቱ ከፍ እንደሚል ይጠበቃል፡፡

የአቶ ደረጀን ሃሳብ የምትጋራው፤ በሽሮ ሜዳ የባሕል ልብስ ሱቅ ባለቤቷ ወይዘሪት አልማዝ ታዬ ነች፡፡ “ለሥራ የሚሆን ምቹ ሁኔታ ባልተፈጠረበትም አካባቢ፤ ቀዳዳዎችን ፈልጎ ለመለወጥ ጥረት ማድረግ ይገባል” በማለት፤ የራሷን ሱቅ ከፍታ፣ ለሌሎች የሥራ ዕድል ፈጥራ፣ ነገን የተሻለ ለማድረግ አቅዳ የምትንቀሳቀስበት ደረጃ ላይ ለመገኘት ያለፈችባቸውን መንገዶች ታስታውሳለች።፡ በትውስታዋ ሌሎችን የሚያበረታ ውጤታማ ተሞክሮ ይንጸባረቃል። ይህች የሥራ ሰው፤ በአዲስ አበባ ነው ተወልዳ ያደገችው፡፡ እስከ 10ኛ ክፍል ከተማረች በኋላ፤ ‘የራሴን የንግድ ድርጅት ማንቀሳቀስ አለብኝ’ የሚል ሕልም ሰንቃ ለማሳካት አንድ ብላ ጀመረች፡፡ በሽሮ ሜዳ ያሉ ሱቆችን የማፅዳት፣ የሽያጭ አጋዥ በመሆን በትጋት መሥራቷን ቀጠለች። ከዚህ ጎን ለጎንም ሙያ ተማረች፡፡ ከቤተሰቦቿ ጋር እየኖረች የምታገኘውን እቁብ እየጣለች እና እያጠራቀመች ለራሷ ሥራ ማስጀመሪያ ጥሪት አካበተች፡፡ በመጨረሻም የራሷን ሱቅ የመክፈት ደረጃ ላይ ደረሰች፡፡

“እንኳን ከመልካም ሁኔታ፤ ከአስቸጋሪ መሰናክል ውስጥም ሥራን መፍጠርና ማከናወን ይቻላል” የምትለው፤ ያለችውንም በተግባር ያረጋገጠችው ወይዘሪት አልማዝ፤ የምሽት ሥራ እንደከተማ በስፋት መተግበሩን ታደንቃለች፡፡ ምሽት ሲሆን በአካል መጥቶ የሚገዛ ሰው ያን ያክል ባይሆንም፤ በሂደት የምሽቱ የሥራ እንቅስቃሴ ከቀኑ ያልተናነሰ እንደሚሆን ተስፋዋን ገልጻለች። ከኢትዮጵያ ውጪ የሚኖሩ ወገኖቻችን የሀገር ባሕል ልብስን የመጠቀም ልምዳቸው ከፍተኛ እንደሆነ በማንሳት፤ በኦንላይን የመረጃ ልውውጥ በማድረግ ልብሶችን አዘጋጅታ የምትልክበት የተለመደ አሠራር ስላላት፤ ይህንን ተግባር በአብዛኛው የምትከውነው አመሻሽ ላይ ነው፡፡ በቅርቡ የተጀመረው የምሽት ሥራ ለእሷ አዲስ እንዳልሆነ አስረድታለች፡፡

በአራት ኪሎ በአዲስ ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁትን በመሬት ውስጥ እና ከመሬት በላይ ያሉትን የግብይት ማዕከላት ጨምሮ ነባሮቹ የንግድ እና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በተነቃቃ የሥራ እንቅስቃሴያቸው አካባቢውን የበለጠ እያደመቁት ይገኛሉ፡፡ በቀንም ሆነ በምሽት  ተመሳሳይ የሥራ ድባብ እንዲኖረው ተደርጎ በተገነባው የ4 ኪሎ ፕላዛ ከሚገኙት የመሬት ውስጥ ሱቆች መካከል በአንዱ የሞባይል ስልኮችንና መለዋወጫዎችን በመሸጥ ሥራ ላይ  ተሰማርቶ ያገኘነው ወጣት ግርማ ጎይቶም ስለምሽት የሥራ እንቅስቃሴ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቶናል፤ “እኔ እንደወጣት ሠርቶ መለወጥ ነው ዋና ትኩረቴ፡፡ ለመለወጥ ደግሞ ሥራንና የሥራ ጊዜን መምረጥ አያስፈልግም። አሁን ያለሁበት የሥራ ቦታ፣ ሥራዬን በሚገባ እንድሠራ ምቹ ሁኔታን ፈጥሮልኛል፡፡ ሥራውን ከወንድሜ ጋር ነው የምንሠራው፡፡ በየተራ እየተቀያየርን በቀንና በምሽት በሱቃችን እንገኛለን፡፡ ደንበኞቻችንም በሚገባ እናስተናግዳለን። የምሽት ሥራው በቀጣይ በነዋሪው እየተለመደ ሲመጣ፤ የተሻለ ጥቅም እንደምናገኝ አምናለሁ፡፡”

በመሐል አራት ኪሎ፤ በአዲሱ ታክሲ ተራ አካባቢ የሚገኘው የተስፋ ቡና ምሽት ላይ ጥሩ የሚባል አገልግሎት እንደሚሰጥ ተመልክተናል፡፡ ምሽት 2፡00 ሰዓት አካባቢ በቤቱ ተገኝተን እንደታዘብነው፤ ወንበሮቹ ቡናና ሻይ በሚጠጡ ደንበኞች ተሞልቷል፡፡ ደንበኞቹ በአብዛኛው በወጣት ዕድሜ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል ወጣት ቴዎድስ ጋሻው እና ወጣት ሄኖክ ደጀኔ የተስፉ ቡና በምሽት ስለሚሰጠው አገልግሎት እና ተጠቃሚነታቸውን ጠይቀናቸው ሃሳባቸውን አካፍለውናል። እነሱ እንዳስረዱት፤ የተስፋ ቡና ተጠቃሚነታቸው የቆየ ነው፡፡ የሥራ ቦታቸው የአንዱ መገናኛ፣ የአንዱ ደግሞ ሜክሲኮ በመሆኑ አራት ኪሎ ከሥራ እንደወጡ ይገናኛሉ፡፡ የሚገናኙት ደግሞ እዚህ ቤት ነው፡፡ የቀደመ ይጠብቃል። የዘገየም ወደዚያው ይሄዳል። እዚህ ተገናኝተው ሻይ ቡና እየጠጡ እና ስለውሏቸው እየተጫወቱ ይቆያሉ። ከዚያም ጉዟቸውን ፈረንሳይ አካባቢ ወደሚገኘው ቤታቸው ያደርጋሉ፡፡

በቀን እና ሌሊት ያልተወሰነ የሥራ እንቅስቃሴ የከተሞች አንድ መገለጫ ባሕርይ ነው፡፡ በዓለም ላይ አሉ የሚባሉ ከተሞች ልምድ የሚያሳየውም ይህንኑ ነው፡፡ ይህን ማድረጋቸው የበዛ ጥቅም እንዲያገኙ እንደሚያግዛቸው የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በጎርጎሮሳዊያን የዘመን ቀመር በወርሃ ጥር 2024 “Rethinking 24-hour cities: night-time strategies to address urban challenges and thrive” በሚል ርዕስ ተዘጋጅቶ የቀረበን ጥናታዊ ጽሑፍ መረጃ እንመልከት፡፡ መረጃው በዋናነት ትኩረት ያደገው፤ “እንቅልፍ አልባዋ ከተማ (The City That Never Sleeps)” በመባል የምትታወቀውን፤ ኒው ዮርክ ነው፡፡ ይህች ከተማ 24/7 ንቁ ነች፡፡ የፋይናንስ ተቋማቷ ለአፍታም ሥራ አያቆሙም፡፡ የተለያዩ ምርትና አገልግሎቶች በፈለጉበት ቅፅበት ይገኝባታል፡፡ የምግብ እና መጠጥ ቤቶች በራቸው አይዘጋም፡፡ ቁርስ፣ ምሳ እና እራት በሚል ለምገባ የተቀመጠ የተለመደ ጊዜ እዚህ አይሠራም፡፡  ምግብና መጠጥ ባስፈለገው ሰዓት መጠቀም የሚችልበት ሁኔታ ስለተመቻቸ፤ ውስጡ በፈለገበት ሰዓት ወደ ምግብ ቤቶቹ ጎራ ብሎ ወይም ካለበት ቦታ አስመጥቶ መጠቀም ይችላል፡፡ በዚህም ኒው ዮርክ በሌሊት በምታደርገው የነቃ እንቅስቃሴ ብቻ በየዓመቱ ከ35 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት ችላለች፡፡ ከ30 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎችም የሥራ ዕድል ለመፍጠር በቅታለች፡፡

እንደ ለንደን፣ ቶኪዮ፣ ሆንክ ኮንግ፣ ዱባይ፣ ባንኮክ፣ ኢስታንቡል የመሳሰሉ የአውሮፓ እና የእስያ ሀገራት ከተሞች በሌሊት የነቃ የሥራ እንቅስቃሴ ከሚታወቁት መካከል መሆናቸውን ይህ የጥናት ፅሁፍ ጠቅሷል፡፡ ከአፍሪካም የናይጄሪያዋን ሌጎስ፣ የደቡብ አፍሪካዋን ጆሃንስበርግ በምሳሌነት አንስቷቸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዓለም አቀፋዊነትና ተወዳዳሪ የንግድ ከተማ እንድትሆን በከተማ አስተዳደር ደረጃ ከተሠሩና እየተሠሩ ካሉ ተግባራት መካከል፤ የመዲናዋ የቀንም ሆነ የምሽት የሥራ እንቅስቃሴ የተነቃቃና ውጤታማ ማድረግ ነው፡፡ የምሽት ንግድን ውጤታማ ለማድረግ የኮሪደር ልማቱን ጨምሮ ከተከናወኑ መሬት ላይ ከሚታዩ የልማት ሥራዎች በተጨማሪ፤ የሕግ ማዕቀፍ (የምሽት ንግድ ደንብ ቁጥር 185/17) አዘጋጅቶ ተፈጸሚ ማድረግም ተችሏል፡፡

በከተማዋ የሚገኘው የንግዱ ማህበረሰብ የወጣውን የምሽት ንግድ ደንብ አክብሮ እንዲሁም እንደከተማ የተመቻቸውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ የምሽት ንግድ ሥራውን በሚገባ እንዲያከናውን የከተማ አስተዳደሩ ያልተቋረጠ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ላይ ነው፡፡ ለአብነት በወርሃ ሐምሌ አጋማሽ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ፣  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊድያ ግርማ እና ከሌሎች የከተማና የክፍለ ከተሞች አመራሮች በጋራ በመሆን በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ተገኝተው የምሽት ንግድ ሥራዎች በምን ሁኔታ እየተከናወነ እንደሆነ ክትትል ያደረጉበት፣ ክፍተቶችንም ለመድፈን የሚያስችል አመራር ለመስጠት ግብዓት የተገኙበትን ተግባር መፈጸማቸውን ማንሳት ይቻላል።

በመዲናዋ የምሽት የንግድ ሥራ በይፋ መከናወን ከጀመረ አራት ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ በእነዚህ ወራቶች ያለውን እንቅስቃሴ፣ የታዩ ውጤቶች፣ ያጋጠሙ ችግሮች እና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን አስመልክቶ የዝግጅት ክፍላችን ላነሳው ጥያቄ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ እንደሳቸው ገለፃ፤ እንደ ከተማ አስተዳደር የወጣው  የምሽት ንግድ ስራዎች ደንብ ቁጥር 185/17 በሥራ ላይ መዋል ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የምሽት ንግድ ሥራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በተለይ በዋና ዋና መንገዶች ላይ ያሉ፣ በኮሪደር ልማቱ የመንገድ መብራት አገልግሎት ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ሥራው እንዲከናወን ግድ ይላል። በዚሁ መሰረት በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ የንግድ ተቋማት የምሽት ንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ይሁን እንጂ የምሽት ንግድ ሥራ እንቅስቃሴ ውስጥ በተገባ በመጀመሪያዎቹ ቀናት እና ሳምንታት ከመብራት መቆራረጥ፣ ከፀጥታ እና ከትራንስፖርት አገልግሎት ጋር የተያያዙ ችግሮች በተወሰነ መልኩ በመታየታቸው ሥራው ላይ የተወሰነ ክፍተት ታይቶ እንደነበር አንስተዋል፡፡

ከንግድ ማህበረሰቡ እንዲሁም በየደረጃው ካሉ የድጋፍና ክትትል ሰጪ ሠራተኞች የመጣውን አስተያየት መነሻ በማድረግ፤ የምሽት ንግድ ሥራው በተሳካ ሁኔታ የሚከናወንበትን መደላድል ለመፍጠር የንግድ ቢሮን ጨምሮ፣ ሠላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ፣ የመብራት ኃይል አገልግሎት እና የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች በጋራ በመሆን በምሽት በመንቀሳቀስ በመሬት ላይ ያለውን ሁኔታ መመልከታቸውን ወይዘሮ ሀቢባ አስታውሰዋል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች (የመብራት መቆራረጥ፣ የፀጥታ ስጋት እና የትራንስፖርት እጥረት) በዋናነት በከተማዋ ዳር አካባቢዎች የታዩ ሲሆኑ፤ እነዚህን ከሥር ከሥር ፈጣን ምላሽ መሰጠቱንም አስረድተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የምሽት የሥራ እንቅስቃሴው የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በዚህ ሥራ ደግሞ ዋነኛ ተጠቃሚው የንግዱ ማህበረሰብ በመሆኑ ሥራውን አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ሸማቹ ማህበረሰብም፤ በተለይ የመንግስት እና የግል ተቋማት እንዲሁም የኢንዱስትሪ ሠራተኞች ቀን ሠርተው ምሽት ላይ ግብይት ለመፈፀም ምቹ ሁኔታ ስለተፈጠረ ይህንን መጠቀም እና ልምዱን ማዳበር ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

የሸማቹ ማህበረሰብ ምሽት ላይ ወደ ንግድ ተቋማት በመሄድ ግብይት መፈፀም ላይ አሁንም ክፍተት እንዳለ የጠቆሙት ቢሮ ኃላፊ፤ ሥራውን በተጣበበ ጊዜ ለሚያከናውን ወይም ቀን ላይ ከቤት ወጥቶ ግብይት ለመፈፀም ለማይችል የከተማዋ ነዋሪ፤ የምሽት ግብይት መጀመር ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ስለሆነ ይህንን አጋጣሚ በአግባቡ መጠቀም ይገባዋል፡፡ የምሽት ግብይት አንዱ የከተሜነት መገለጫ በመሆኑ ከዚህ አሠራር ጋር መላመድ እንደሚያስፈልግም መክረዋል፡፡ 

በወቅቱ በምልከታችን፤ የምሽት ንግድ ላይ የተሠራው የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ፣ ደንቡን ለማስፈጸም ከላይ እስከ ታች የተደረገው ድጋፍ እና ክትትል እንዲሁም የንግዱ ማህበረሰብ በምሽት ንግድ እንቅስቃሴው ላይ በንቃት ለመሳተፍ ያሳየው ቁርጠኝነት የሚያበረታታ ውጤት የታየበት መሆኑን አመራሮቹ ተናግረዋል። በሌሎች ክፍለ ከተሞችም መሰል የአመራር ክትትልና ድጋፍ መደረጉን እንዲሁም በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ከአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በደረጀ ታደሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review