ኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳልያ ለማግኘት የቀራት ብቸኛ ውድድር የወንዶች 5000 ሜትር

You are currently viewing ኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳልያ ለማግኘት የቀራት ብቸኛ ውድድር የወንዶች 5000 ሜትር

AMN-መስከረም 11/2018 ዓ.ም

በቶኪዮ እየተደረገ የሚገኘው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ የተለመደውን ዓይነት ውጤት እየገኘች አይደለም።

ሁለት ብር እና ሁለት ነሃስ ያስመዘገበችው ኢትዮጵያ ወርቅ የማሳካት ብቸኛ እድሏ ቀን 7፡47 በሚደረገው የወንዶች 5000 ሜትር ውድድር ላይ የተንጠለጠለ ነው፡፡ እኤአ 1993 ላይ ሀይሌ ገብረስላሴ ወርቅ ካመጣ በኋላ ኢትዮጵያ በ15 ተከታታይ ሻምፒዮና ላይ ቢያንስ አንድ ወርቅ ሜዳልያ አምጥታለች፡፡

ኢትዮጵያ በዛሬው ውድድር ልምድ ባካበተው ሀጎስ ገብረሕይወት እና በወጣቱ አትሌት ቢንያም መሀሪ ትወከላለች፡፡ የ31 ዓመቱ ሀጎስ ገብረሕይወት ሀገሩን በታላላቅ መድረክ ለ10ኛ ጊዜ ይወክላል፡፡

አትሌቱ በ5000 ሜትር በኦሊምፒክ አንድ ነሃስ ፤ በዓለም ሻምፒዮና ደግሞ አንድ ብር እና አንድ ነሃስ ማግኘት ችሏል፡፡ ሀጎስ ከመም (ትራክ) ሳይወጣ ለሀገሩ የወርቅ ሜዳልያ የማምጣት እቅድ አለው፡፡ ይህን የማሳካት እድሉ ከዛሬ የሚያልፍ አይመስልም፡፡

በተለይ ኢትዮጵያ ወርቅ ለማግኘት በተቸገረችበት ሰዓት ይህን ማሳካት ከቻለ ስሙን ዘላለማዊ ማድረጉ አይቀርም፡፡ ማጣሪያ ላይ ያሳየውን ድክመት ግን መቅረፍ ይኖርበታል፡፡

ገና 18 ዓመቱ ላይ የሚገኘው ቢንያም መሀሪ ለወደፊት ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት ቢሆንም ለዛሬው ውድድርም በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡

ማጣሪያውን አንደኛ ወጥቶ ያለፈበት በራስ መተማመን ለፍፃሜው ውድድር እንዲጠበቅ አድርጎታል፡፡ የልምድ ማነስ ካልገደበው በስተቀር ለሀገሩ ሜዳልያ የማምጣት እድል እንዳለው አሳይቷል፡፡

በቶኪዮ እየተደረገ የሚገኘው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ በይፋ ይጠናቀቃል፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review