የሀገርን ህልውናና ብሔራዊ ጥቅሞች ለመጠበቅና ለማስከበር ሠራዊቱ ከምንግዜውም በላይ ዝግጁ ነው ሲሉ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ

You are currently viewing የሀገርን ህልውናና ብሔራዊ ጥቅሞች ለመጠበቅና ለማስከበር ሠራዊቱ ከምንግዜውም በላይ ዝግጁ ነው ሲሉ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ

AMN መስከረም 11/2018

የሀገርን ህልውናና ብሔራዊ ጥቅሞች ለመጠበቅና ለማስከበር ሠራዊቱ ከምንግዜውም በላይ ዝግጁ መሆኑን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።

የሁርሶ የዕጩ መኮንን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ዛሬ ለ26ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን ዕጩ መኮንኖች በደመቀ ስነ-ስርዓት አስመርቋል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በስልጠናው ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ተመራቂዎች ሽልማት ያበረከቱ ሲሆን ለተመራቂዎቹ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።

ፊልድ ማርሻሉ በመልዕክታቸው እንዳሉት ሠራዊታችን የትኛውንም ተልዕኮ በብቃትና በቁርጠኝነት መወጣት የሚያስችለው የዘመኑን ወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ ቀስሟል።

ውትድርና ሳይንስም ጥበብም ነው ያሉት ፊልድ ማርሻሉ፤ ተመራቂዎች በቀሰማችሁት የንድፍና የተግባር ስልጠና ከፍ ብላችሁ እንደ ንስር በመብረር ለሀገር ከፍታና ሉዓላዊነት መስራት ይኖርባችኋል ብለዋል።

ሀገራችን የተፈጥሮ ሃብቷን እንዳትጠቀም የሚፈልግ ጠላት እንዳላት ጠቅሰው፤ ይሄ ጠላት ባንዳ በመመልመልና የውስጥ ቀዳዳን በመፍጠር አገርን ለማተራመስ እየተራወጠ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ይህን ታላቅ ህዝብና ሀገር የሚመጥን ዘመናዊ ሰራዊት ገንብተን የሀገርን ብሔራዊ ጥቅሞች በአስተማማኝ መንገድ የመጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነታችንን እየተወጣን ነው ብለዋል።

የዛሬ ተመራቂዎች በቀሰሙት ዕውቀትና ጥበብ በመታገዝ የአገርን ሉዓላዊነት በመጠበቅና በማስከበር የአባቶችን ፈለግ መከተል እንዳለባችውም አስገንዝበዋል።

በተለይም በስልጠናው በቀሰሙት እና ቀድሞ ባካበቱት ወታደራዊ ልምድ በመታገዝ እንደ ንስር ከፍ ብላችሁ በመብረር ሠራዊቱን የመምራት ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ አሳስባለሁ ብለዋል።

የሰራዊት ግንባታው ስራ ፍሬ እያፈራ መሆኑን ዛሬ በምረቃው ላይ በአግባቡ መመልከታቸውንም ፊልድ ማርሻሉ ተናግረዋል ።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review